መጋቢት ፳( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጋዜጠኛ አንዱአለም ሲሳይ ታዋቂውን የኢኮኖሚክ ፕሮፌሰር ዶ/ር አለማየሁ ገዳን ያቀረቡትን ጥናታዊ ጥሁፍ በመጥቀስ እንደዘገበው የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ብድር ላይ ያለው ፍላጎት እየጨመረ መምጣት ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኑዋል፡፡
ፕ/ር አለማየሁ ጥናታቸውን ያቀረቡት የማህበራዊ ጥናት መድረክ ባዘጋጀው ውይይት ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከቻይና 17 ቢሊዮን ዶላር፣ ከቱርክ 3 ቢሊዮን ዶላር፣ ከህንድ 1 ቢሊዮን ዶላር፣ ከአለም ባንክ 6 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በቅርቡ ከአውሮፓ ዩሮ ቦንድ 1 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ዶላር መበደሩዋን የተናገሩት ፕ/ር አለማየሁ፣ በወጪ ንግዱና በገቢ ንግዱ መካከል ያለውን 10 ቢሊዮን ዶላር ክፍተት የሚሞሉት እነ ቻይና ናቸው ብለዋል፡፡
ቻይና ድጋፉዋን በድንገት ነገ ብታቁዋርጥ ምን ይፈጠራል፣ ቻይና ኢትዮ ቴልኮምን ወይም አየር መንገድን ካልሸጣችሁ ወይም የአክሲዮን ድርሻ ካልሰጣችሁኝ ድጋፌን አቆማለሁ ብትል ምን ይፈጠራል; አገሪቱ ሙሉ በሙሉ ሙሉ በሙሉ እንደምትንኮታኮት አረጋግጥላችዋለሁ ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡
የቻይና የህንድ ወይም የቱርክ ኢንቨስትመንት ስራ በመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማምጣት እንዲሁም ምርትን ወደ ውጭ በመላክ የሚገኝን ገቢ በመጨመር በኩል ያለው ጠቀሜታ እጅግ አነስተኛ ነው ያሉት ፐ/ር አለማየሁ፣ በፈረንጆች አቆጣጠር ከ2003 እስከ 2012 93 የቻይና ኩባንያዎች 600 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርገው፣ ለ69 ሺ ሰዎች በቁዋሚነት እና ለ79 ሺ ሰዎች ጊዚያዊ ስራ ቢፈጥሩም ፣ ቴክኖሎጂን በማሸጋገርና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ድርሻቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡
ፕ/ር አለማየሁ፣ ከደቡብ ኮሪያውያን በመማር በጊዜ ከዳ መውጣት እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ዘገባው የኢትዮጵያን እድገት በተመለከተ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የሚሰጡት መግለጫ እርስ በርስ የሚጣረስ መሆኑንም አመልክቱዋል፡፡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ኢኮኖሚው በ7 በመቶ ሊያድግ ይችላል ሲሉ፣ አማካሪያቸው አቶ አርከበ እቁባይ ደግሞ በ11 በመቶ ያድጋል ብለዋል፡፡