ኢትዮጵያ ወታደሮቿ ከሶማሊያ ለቀው ለመውታጣቸው አለም አቀፍ ማህበረሰብ ተጠያቂ አደረገች

ኢሳት (ጥቅምት 26 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ተሰማርተው የሚገኙ ወታድሮቿ ከቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው ለመውጣታቸው የአለም አቀፍ ማህበረሰብን ተጠያቂ አደረገች።

በተያዘው የጥቅምት ወር ብቻ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶስት ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው የወጡ ሲሆን፣ የሶማሊያ ታጣቂ ሃይል አልሸባብ ሶስቱን ስፍራዎች ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የአለም አቀፍ ማህበረሰብ መስጠት የነበረበትን ድጋፍ ባለመስጠቱ ምክንያት ክፍተት መፍጠሩንና ታጣቂ ሃይሉ አልሸባብ ይህንኑ አጋጣሚ ሊጠቀም መቻሉን ገልጸዋል።

የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሶማሊያ ብሄራዊ ጦርን ለመደገፍ ቃል ቢገባም በተግባር የሚጠበቀውን ያህል እንዳልታየ ለቢቢሲ ምላሽን ሰጥተዋል።

የተለያዩ አካላት ኢትዮጵያ ወታደሮቹ ከሶማሊያ እያስወጣች ያለችው በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው ረዳ እርምጃው ከአዋጁ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ያስታወቁ ሲሆን፣ በማዕከላዊ ሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቲየግሎ፣ ኤል አሊፍ እና ሃልጋን ከሚብጋሉ ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው መውጣታቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ወታደሮች ይዞታቸውን ለቀው መውጣታቸው በሶማሊያ ተሰማርቶ የሚገኘውን የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይል አደጋ ውስጥ ሊከተው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

ኢትዮጵያ ከአራት ሺ የሚበልጡ ወታደሮቿን በህበረቱ የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር አሰማርታ የምትገኝ ሲሆን፣ ቁጥሩ የማይታወቅ ተጨማሪ ወታደርን በተናጠል በማሰማራት ከአልሸባብ ታጣቂ ሃይል ጋር ግጭት ውስጥ መቆየቷ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ የተውጣቱ ወደ 20 ሺ አካባቢ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በሶማሊያ ተሰማርተው ቢገኙም አልሸባብ አሁንም ድረስ የሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት ሆኖ ይገኛል።

ለዚሁ የሰላም አስከባሪ ሃይል የገንዘብ ድጋፍን ሲያደርግ የቆየው የአውሮፓ ህብረት ከወራት በፊት የሚሰጠውን ድጋፍ በ20 በመቶ አካባቢ እንዲቀንስ ማድረጉ ይታወሳል።

ህብረቱ የወሰደው ውሳኔ ተከትሎ ኬንያ እና ዩጋንዳ እርምጃውን በመቃወም የደጋፍ መቀነስ በሰላም አስከባሪ ሃይሉ ላይ ተፅዕኖን ያሳድራል ሲሉ ቅሬታን አቅርበዋል።

የዩጋንዳ መከላከያ ሰራዊት በበኩሉ በቀጣዩ የፈረንጆች አመት ወታደሮቹን ከሶማሊያ ጠቅልሎ እንደሚያስወጣ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

ከስድስት ወር በላይ ውዝፍ ጥቅማጥቅም ሳይከፈላቸው የቆዩ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ከአውሮፓ ህብረት በተሰጠ የገንዘብ ድጋፍ ክፍያ እየተሰጣቸው መሆኑም ታውቋል።

ይሁንና የፖለቲካ ተንታኞች የሰላም አስከባሪ ቀጣይ እጣ ፈንታ አደጋ ውስጥ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው።