ኢትዮጵያ ከአለማቀፍ የገንዘብ ገበያ ለመበደር ድርድር ጀመረች

ኀዳር ፲፯(አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :- መንግስት የጀመራቸውን የሃይል፣ የመንገድ፣ የባቡርና የስኳር ፋብሪካዎችን ለመጨረስ የሚያስችለውን ገንዘብ ከአለማቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ለመበደር የሚያስችለውን ድርድር ከሁለት የአውሮፓ እና ከአንድ የአሜሪካ ባንክ ጋር ጀምሯል። መንግስት ገንዘቡን ለመበደር የሚያስችለውን ቦንድ ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፣ አለማቀፍ አበዳሪ ተቋማትም የመንግስትን የመክፈል አቅም በማየት ብድሩን ይፈቅዳሉ።

መንግስት ከአለማቀፍ የግል አበዳሪ ድርጅቶች ገንዘብ ለመበደር ወደ አለማቀፍ የካፒታል ገበያ ሲገባ ይህ የመጀመሪያው ነው። ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከመንግስታት እንዲሁም ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋምና ከአለም ባንክ በአነስተኛ ወለድ ብድር ስታገኝ ቆይታለች። ይሁን እንጅ ከእነዚህ ተቋማትም ሆነ ከኤክስፖርት  የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ  አነስተኛ መሆን የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ለማስፈጸም ባለማስቻሉ መንግስት ከአለማቀፍ የግል አበዳሪ ድርጅቶች ለመበደር በመወሰን ድርድር ጀምሯል።

መንግስት ወደ አለም የገንዘብ ገበያ ለመግባት መወሰኑን ተከትሎ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ይሰጣሉ። በአንድ በኩል መንግስት የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች ለመጨረስ ብድሩ አስፈላጊ መሆኑን የሚከራከሩ ወገኖች ያሉትን ያክል፣ ብድሩ ኢትዮጵያን ልትወጣው በማትችል እዳ ውስጥ ይከታትና የሁላ ሁላ ችግር ያመጣባታል ብለው የሚሰጉም አሉ።

ታዋቂ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ፕ/ር ሰኢድ ሃሰን፣  ሚንጋ ነጋሽ፣ ተስፋየ ለማና አቡ ግርማ ሞገስ በጋራ ባወጡት ጥናታዊ ጽሁፍ የመንግስት ውሳኔ ችግሮችን ሊያመጣ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። የኢትዮጵያ እዳ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ አገሪቱ ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው ገቢ ጋር የማይጣጣም መሆኑ ሊያሳስብ እንደሚገባ የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።መንግስት የሚወስደውን ገንዘብ ለየትኛው ፕሮጀክት በትክክል ማዋል እንዳለበት እንዲሁም ተጨባጭ የሆነ የፋይናንስ እቅድ ማዘጋጀት እንደሚኖርበት ባለሙያዎች ምክራቸውን ለግሰዋል።

ኢትዮጵያ ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ እዳ እንዳለባት መረጃዎች ያሳያሉ።