ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ጦርነት ማብቃቱን በይፋ ከማወጅም አልፈው በበርካታ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነቶችን ተፈራረሙ።
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 2 ቀን 2010 ዓ/ም)ነገሮች ሁሉ ህልም እንጂ እውን አይመስሉም።እየሆነ ባለው ተዓምር ብዙዎች እጃቸውን አፋቸው ላይ ጭነዋል።በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን መስዋዕት የሆኑበት ፣ በሚሳይል እና በላውንቸር ሊቋች ያልቻለው እና ለ20 ዓመት ተበግሮ የዘለቀው የጥላቻ ግንብ “ድንበራችን ፍቅር ነው” በሚል የፍቅር ቃል ተናደ።
ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጲያን ጠቅላይ ሚኒስተርን የያዘ ቦይንግ 787 የኢትዮጲያ አውሮፕላን የኤርትራን አየር ክልል ጥሶ የገባው ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ሌሊት ነበር። ንጋት ላይ አስመራ በሰላም ማረፉን ታማኝ ምንጮች ቀድመው ዘገቡ።
እንደምንጮቹ ገለጻ፣ ጉዞው ሚስጥራዊ የተደረገበት ምክንያትም፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደህንነት ተብሎ እንደሚሆንም ተገምቷል።
በዚህ ዕለት ዋዜማ የስልክ መስመር ተከፍቶ አስመራ እና አዲስ አበባ ማውራት ጀምረዋል። ዓመታት የተነፋፈቁ ዘመዶችና ጓደኛሞች ተገናኝተው ያለሥጋት በነጻነት አውርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አስመራ ሲገቡ ፣ ላለፉት ረዥም ዓመታት ሢስቁ ያልታዩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቄን ጨምሮ ከፍተኛ የኤርትራ ባለሥልጣናት በልዩ ፈገግታና በአክብሮት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ለረዥም ዓመታት ፍቅርን የጠራቡና የተጠሙ፣ በወገኖቻቸው ናፍቆት የተሰቃዩ ኤርትራውያን ዓለምን ባስደነቀ ሁኔታ ለዶክተር አብይ አሕመድ እጅግ ደማቅ የፍቅር አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት አቶ እስጢፋኖስ በትዊተር ገጻቸው እንደገለጹት፣ እስካሁን በኤርትራ የዶክተር አብይን ያህል ደማቅ አቀባበል የተደረገለት መሪ የለም።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አብረው ከተጓዙት መካከል በሕዝቡ ሁኔታ እጅግ የተደነቁት የህወሓቷ ወይዘሮ ከይሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው ” የአስመራ ሕዝብ ያለው የሰላም ፍላጎትና ምኞት ምን ያክል ጥልቀትና ሥፋት እንዳለው ስታይ፤ እንኳን ለ20 ዓመት ይቅርና ለ10 ደቂቃም መለያየት አይገናባንም ነበር። ሁኔታው እሱን ነው ለእኔ ያስተማረኝ።”ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በበኩላቸው፦<<ዛሬ በአስመራ የወጣው ህዝብ ምን ያህል የምር እኛ ኤርትራዊያን ኢትዮጵያዊያንን እንፈለጋቸውና እንወዳቸው እንደ ነበር ያስመሰከረ ነው። ዛሬ የኤርትራ ህዝቡ የልቡን ፍላጎት መቆጣጠር ተስኖት የአስመራን መንገዶች በደስታ ሲቦርቅባቸው ውሏል። እኔ ምን ማለት እችላለሁ? እውነተኛ የህዝቡ ስሜት እንደሆነ አያችሁት እኮ! ለ25 አመታት ለሰላም በር ተዘግቶብን ነበር፤ 25 አመታት ከስረን ነበር። አሁን ግን አልከሰርንም፤ ዓብይ ለዚህ ዋጋ ከፍሏል። ከዚህ በኋላ ምንም ይምጣ ምን፣ ከዓብይ ጋር በጋራ እንወጣዋለን፣ አብረን እናልፋለን፣ የሚያግደን ነገር የለም አይኖርምም። ወደእሁ! ጨረስኩ!>>ብለዋል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎችና ሌሎች ባለሥልጣናት ቡና እየጠጡ ልባዊ በሆነ ፈገግታ ሢጫዎቱ፣ ሀሳበ ትልቅ የሆኑት እና በእድሚያቸው ከሁሉም የሚያንሱት ዶክተር አብይ እንደልጅነታቸው በህትና የቡና ቁርስ ሲያድሉ፣ ተራራ ስር ባለ ነፋሻማ ስፍራ እንደተነፋፈቀ ጓደኛ በለስ እየበሉ በደስታ ሲያወጉ ታዩ።
በዚህም ሳያቆሙ “ፍቅር መዝሙራችን፣አንድ ነው ደማችን።” በሚል ዜማ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ሲወዛወዙ ታዩ።
ሁለቱ መሪዎቹ በዛሬው ዕለትም ጦርነት ማቆምን በይፋ ከማወጅ ጀምሮ በማህበራዊው በኢኮኖሚያዊውና በጸጥታው ዘርፍ አብሮ ለመሥራት በርካታ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ከስምምነቶቹ መካከል ኢትዮጵያ በጣም ፍትሃዊ በሆነ ዋጋ በአሰብ ወደብ እንድትጠቀም አዲስ አበባ እና አስመራ ያሉ ኤምባሲዎች እንዲከፈቱ እና የዲፕሎማሲ ስራቸውን እንዲጀምሩ፣ የየብስ ትራንስፖርትን ጨምሮ የሁለቱም አገራት አየር መንገዶች ወደየሀገራቱ በረራ እንዲጀምሩ፣ የተጀመረው የስልክ አገልግሎት እንዲቀጥል እና የሁለቱም ሀገራት አርቲስቶች በአስመራ እና በአዲስ አበባ የፍቅር እና የሰላም ኮንሰርት እንዲያዘጋጁ የሚሉት ይገኙበታል።
የጥልን ግንብ በመናድ በሀገራቱ መካከል ጠንካራ የፍቅር ድልድይ እንዲገነባ መሰረት የጣሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ዛሬ ረፋዱ ላይ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ እና በከፍተኛ የኤርትራ ባለሥልጣናት የክብር አሸኛኘት ተደርጎላቸው በሰላም አዲስ አበባ ገብተዋል።