ኢትዮጵያ ኢንተርኔት ስለላ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር አውጥታለች ተባለ

ኢሳት ዜና (ሐምሌ 6 2007)

የኢትዮጵያ መንግስት ከጣሊያኑ የሳይበር ሴኩሪቲ ኩባኒያ ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ሲገልጽ ቢቆይም የኩባኒያው ሀላፊዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት ሰኞ ማረጋገጫ መስጠታቸውን የእንግሊዙ ዘጋርዲያን ጋዜጣ ዘገበ።

የሀኪንግ ቲሙ መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ዴቪድ ቭንሴንዜቲ ድርጅታቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ለግብጽ ለሱዳንና ለሞሮኮ የአፍሪካ ሀገራት አገልግሎቱን ሲያቀርብ መቆየቱን የፋ አድርጓል።

“ኢትዮጵያ አገልግሎታቸንን ጋዜጠኞችንና የመንግስት ተቃዋሚዎችን ለመሰለል መጠቀሟን በሰማን ግዜ ሀገሪቱ ካለፈው አመት ጀምሮ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ተደርጓል” ሲሉ ሀላፊው አስረድተዋል።

በቅርቡ ከኩባንያው በሌላ አካል የተገኘው መረጃ የኢትዮጵያ መንግስት ከኩባንያው አገልግሎቱን ለማግኘት ሲል የአንድ ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ መክፈሉን የሚያሳይ ደረሰኝ ይፋ መደረጉ የታወሳል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከጣሊያኑ የሀኪንግ ቲም ኩባንያ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ማስተባበያን ሲሰጡ ቢቆዩም የድርጅቱ መስራች የሆኑት ዴቪድ ቭንሴንዜቲ ኢትዮጵያ አንዷ ደንበኛ ሆና መቆየቷን ለጣሊያኑ ላስታምፓ ጋዜጣ ይፋ አድርገዋል።

ከአራቱ የአፍሪካ ሀገራት በተጨማሪም ሶሪያን ጨምሮ በተለያዩ የሰባዊ መብቶች ረገጣ የሚታወቁ ሁገራት የኩባንያው ደንበኛ ሆነው መቆየታቸው ታውቋል።

ሰሞኑን በኩባንያው ላይ የተፈጸመው ጥቃትም በድርጅቶች ሳይሆን በመንግስት ደረጃ በተቋቋሙ ሊሆን እንደችል ሚስተር ዴቪድ ቭንሴንዜቲ ለጋዜጣው አስረድተዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የተጠየቀው በዚህ በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢንባሲ በበኩሉ “ ስለ ሪፖርቱ የሚታወቅ ነገር የለም “ ሲል ለዋሺንግተን ፖስት ማስተባበያን ሰጥቶ እንደነበር የታወቃል።

የሁኪንግ ቲሙ ሀላፊዎች የሰጡትን ማረጋገጫ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እስካሁን ድረስ የሰጡት መላሽ የለም።