ኢትዮጵያ ባጋጠማት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ በረዥም ጊዜ ክፍያ ነዳጅ ለማስገባት ሳኡዲ አረቢያን ጠየቀች።

ኢትዮጵያ ባጋጠማት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ በረዥም ጊዜ ክፍያ ነዳጅ ለማስገባት ሳኡዲ አረቢያን ጠየቀች።
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 11 ቀን 2010 ዓ/ም )ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትናንት ረቡዕ ሀገራቸው ካጋጠማት የምንዛሬ እጥረት አንጻር በ12 ወራት ተከፍሎ በሚያልቅ እዳ የነዳጅ ዘይት እንድትሸጥላቸው ለሳኡዲ አረቢያ ጥያቄ እንዳቀረቡ መናገራቸውን፤ ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ብሄት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በበኩላቸው ለዜና አገልግሎቱ እንደተናገሩት በዶላር እጥረትና በቂ የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመዘርጋቱ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን የሚሆኑ ሸቀጣሸቀጦች እና ዕቃዎች በጁቡቲ ወደብ ተከማችተው ተቀምጠዋል።
“የነዳጅ ዘይቱ ግዥ እንዲፈቀድልን ጥያቄ አቅርበናል።ዝርዝሩ በሂደት ይከናወናል። በዚህ ዙሪያ የተያዘው እቅድና ፕሮግራም ኢምፖርት ማድረግ የምንችለውን ለመተንበይና ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ለመቆጠብ ያስችለናል።” ሲሉም አክለዋል።
የዶክተር አብይ አስተዳደር በውጭ ከሚገኙ ዲያስፖራዎች በቀን አንድ ዶላር ለመቆጠብ ያዘጋጀውን የትረስ ፈንድ እቅድ ትናንት ይፋ አድርጓል።
በጅምር ለውጡ የተደሰቱ በርካታ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥሪውን በመቀበል በቀን አንድ ዶላር ለመለገስ መዘጋጀታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።