ኢሳት (ግንቦት 28 ፥ 2009)
የደቡብ ሱዳን የጎሳ መሪዎችና የፓርላማ አባላት ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳንና አማጺ ቡድን መካከል ከሁለት አመት በፊት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በአዲስ መልክ እንዲቀጥል ለማድረግ ገለልተኛ አይደችም ሲሉ ተቃውሞ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ መንግስት የፊታችን ሰኞ በኢጋድ አማካኝነት በደቡብ ሱዳን ላይ የሚመክር ጉባዔ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረቡን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ሰኞ ዘግቧል። ይሁንና ኢትዮጵያ ላቀረበችው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ የደቡብ ሱዳን የዲንቃ ጎሳ ምክር ቤት አመራሮችና የፓርላማ አባላት፣ ኢትዮጵያም ሆነች ኢጋድ አዲስ ድርድር እንዲካሄድ ገለልተኛ አይደሉም ሲሉ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ጋዜጣው አመልክቷል።
በኢትዮጵያ አስተባባሪነት የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የደቡብ ሱዳን መንግስትና በሪክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን የሰላም ስምምነት እንዲደርሱ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይሁንና ሁለቱ ወገኖች የሰላም ስምምነት በደረሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ ግጭት ተቀስቅሶ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ይገኛል። በዚሁ አዲስ ድርድር የምክትል ፕሬዚደንትነት ስልጣን ተሰጥቷቸው የነበሩት ሪክ-ማቻር ከሃገሪቱ በመሰደድ በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ መሆናቸው ታውቋል።
አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ አካላት የተቋረጠው የሁለቱ ወገኖች ድርድር በአዲስ መልክ እንዲቀጥል ግፊትን እያደረጉ ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የፊታችን ሰኞ በአዲስ አበባ ምክክር እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረባቸውን ለመረዳት ተችሏል።
በደቡብ ሱዳን ፓርላማ የሰብዓዊ መብት እና የህገ-መንግስት ጉዳዮች ኮሚቴ ጸሃፊ የሆኑት አልዶ አጆ አኩዬ ኢትዮጵያም ሆነች ኢጋድ ገለልተኛ ባልሆኑበት ሁኔታ እንዴት አዲስ ድርድር ሊካሄድ ይችላል ሲሉ ቅሬታን አቅርበዋል።
የሳልባ-ኪር መንግስት በርካታ ባለስልጣናት ከሁለት አመት በፊት ከአማጺ ቡድን ጋር ተደርሶ የነበረው የሰላም ድርድር በአዲስ መልክ እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳላቸው ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
ይሁንና የአደራዳሪነት ሚናውን እየተጫወቱ ያሉት ኢትዮጵያና ኢጋድ ሲያሻቸው የመንግስት ለውጥ እንዲመጣ አንዳንዴ ደግሞ በሰላም ዙሪያ ቁርጠኝነት ያላቸው መስለው ይቀርባሉ ሲሉ የፓርላማ አባሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ኢጋድ መቼም ቢሆን፣ ገለልተኛ ሆነው አያውቁም ያሉት የፓርላማ አባሉ አልዶ አጆ ዴንግ፣ አዲስ ሊካሄድ የታቀደ ድርድርም ትርጉም አይኖረውም ሲሉ ተቃውሞአቸውን በይፋ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ያሉ የኑዌር አንጃዎች ለጁባ መንግስት ስጋት ፈጥረው የሚገኙ ሲሆን፣ በርካታ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ኢትዮጵያ የሃገሪቱ ተቃዋሚ አካላትን ትደግፋለች ሲሉ ቅሬታን ያቀርባሉ። ይህንኑ ተከትሎ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ከወራት በፊት አንደኛው ሃገር የሌላኛውን ሃገር አማጺ ቡድን ላለመደገፍ ስምምነት አድርገዋል።
የዚሁኑ ስምምነት ተከትሎ ኢትዮጵያ የአማጺ ቡድኑ መሪ ሪክ ማቻር ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ እገዳ ጥላ ትገኛለች።
የአማጺ ቡድኑ አመራሮች በበኩላቸው ኢትዮጵያ የወደደችው ዕርምጃ የስላም ድርድሩ እንዳይቀጥል እንቅፋት ፈጥሯል ሲሉ ይገልጻሉ። ማቻር ከአንድ አመት በላይ በአዲስ አበባ ተቀምጠው ከሃገራቸው መንግስት ድርድርን ሲያካሄዱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። በፓርላማ አባላቱና በሃገር ሽማግሌዎች የቀረበውን ተቃውሞ በተመለከተ ከኢትዮጵያ የተሰጠ ምላሽ የለም።