ኢትዮጵያ በየጊዜው የምትበደረው ገንዘብ ዕዳ የመክፈል አቅሟን እያዳከመ ነው ተባለ

ኢሳት (ሃምሌ 11 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች ሲወስድ የቆየው አለም አቀፍና የሃገር ውስጥ ብድር ዕዳ የአገሪቱን እዳ የመክፈል አቅም እንደሚጎዳ አንድ አለም አቀፍ ተቋም አሳሰበ።

ይኸው የመንግስት የውጭ ዕዳ የመሸከም አቅም እንዲገመገም በመንግስት ተቀጥሮ የነበረውና ፈች የሚል ስያሜ ያለው ኩባንያ የመንግስት የልማት ድርጅቶች እዳ እያሻቀበ መሆኑንና በድርጊቱ በብሄራዊ ደረጃ ስጋት እየሆነ መምጣቱን ይፋ አድርጓል።

ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የሃይል ማመንጫዎች እንዲሁም የትራንስፖርትና የንግድ ስራዎች በመንግስት የልማት ድርጅቶች የተካተቱ ሲሆን፣ እነዚህ ተቋማት ለማጠናከር መንግስት ከፍተኛ የውጭ ብድርን ሲወስድ እንደቆየ ታውቋል።

የመንግስት የውጭ እዳ የመሸከም አቅም ሲያጠና የቆየው ኩባንያ የመንግስት ልማት ድርጅቶች እስካለፈው አመት ድረስ የድርጅቶቹ እና ከሃገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት ጋር ሲነጻጸር የያዙት ድርሻ 29 በመቶ መሆኑን አስታውቀዋል።

የድርጅቶችን የእዳ መጠን መከታተል እንደሚገባ ያሳሰበው ፈች የተሰኘው ኩባንያ የድርጅቶቹ የእዳ ክምችት እንደቀጣይ የሃገሪቱ ዕዳ አድርጎ እንደሚያይ አክሎ መግለጹን በሃገር ውስጥ የሚታተሙ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

መንግስት በበኩሉ ኩባንያው ያቀረበውን ስጋት የተጋነነ በማለት ያስተባበለ ሲሆን፣ አበዳሪዎች ለልማት ድርጅቶቹ ገንዘብ ያበደሩት የመክፈል አቅም እንዳላቸው ተገንዝበው ነው ብሏል።

በቅርቡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሃገሪቱ አጠቃላይ የብድር መጠን ወደ 35 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ መድረሱን ይፋ ማድረጉ የሚታወቅ ነው።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሃገሪቱ የብድር መጠን በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ከሚያመጣው ተፅዕኖ በተጨማሪ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በበኩሉ ሃገሪቱ በተረጋጋ የኢኮኖሚ ሂደት ውስጥ መሆኗን በመግለጽ በባለሙያዎች እየቀረበ ያለን ትችት አስተባብሏል።

ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በተያዘው የፈረንጆች አመት ያድጋል ተብሎ ከተገመተው በታች እድገትን ሊያስመዘግብ እንደሚችል መንግስትና የአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ትንበያን አስቀምጠዋል።