(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 9/2010)ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።
ዶክተር አብይ አሕመድ ከባለሃብቶች ጋር ባካሄዱት ውይይት ላይ እንደገለጹት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት የሚልኩትን የውጭ ምንዛሪ ማቀብ ከፍተኛ ጉዳት አለው።
እናም በውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን መንግስትን ለመቆንጠጥ ብላችሁ የምታደርጉት ርምጃ ሕዝብን እየጎዳ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እንዳሉት የውጭ ምንዛሪ ችግር ለሚቀጥሉት 10 እና 15 አመታት ይቀጥላል።
ችግሩ በአጭር ጊዜ የሚፈታ አይደለም ነው ያሉት።
የውጭ ምንዛሪ ክምችት በሂደት የሚፈጠር በመሆኑም ዋነኛው ችግር ያለውን የውጭ ምንዛሪ እንደ አስፈላጊነቱ በቅደም ተከተል የመጠቀም እጥረት አለብንም ብለዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው የሚልኩት ገንዘብ በጣም ውስን እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ገልጸዋል።
እናም በውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን መንግስትን ለመቆንጠጥ የውጭ ምንዛሪ ከመላክ መቆጠብ ትክክለኛ ቅጣት አይደለም ነው ያሉት።
እንደ ዶክተር አብይ ገለጻ ዲያስፖራው በጽሑፍ፣በሰልፍ፣በንግግር መንግስት ላይ ተጽእኖ ማሳደር ይችላል በውጭ ምንዛሪ ዕቀባ ሲሆን ግን ሀገር ይጎዳል ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አለምአቀፉ የኢትዮጵያውያን የጋራ ግብረ ሃይል በወሰደው ርምጃ በውጭ ምንዛሪ ላይ እቀባ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል።
ዶላርን በጥቁር ገበያ የመመንዘር ችግርም ሌላው የሀገሪቱ ጣጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ወደ ውጭ የሚደረግ ጉዞ በባለስልጣናት ደረጃ ስለበዛ ይህም የሚቀነስበት ሁኔታ እንደሚኖር ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሀገር ሃብት እየዘረፉ በውጭ ገንዘብ የሚያስቀምጡትን በተመለከተም እንደ ቻይና ባሉ ሀገራት እንደሚደረገው በውጭ ያሉ አካውንቶችን የማዘጋት ርምጃ ለመውሰድ እቅድ መኖሩንም ዶክተር አብይ ገልጸዋል።
ከዚሁ የምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውና በአጼ ሃይለሰላሴ ዘመነ መንግስት ስራ የጀመረው ግዙፉ ባምቢስ ሱፐር ማርኬት ሊዘጋ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።