ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ህግና ስርኦቶች መከበር 42 ደረጃ ላይ ተቀምጣለች ተባለ

ኢሳት ዜና (መስከረም 19 ፣ 2008)

በአለማችን የደህንነት ስጋት ይታይባቸዋል ተብለው ከተፈረጁት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በ 42ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያካሄደ አንድ አለም አቀፍ ተቋም ገለጠ።

የዘንድሮውን አመታዊ ረፖርት ይፋ ያደረገው ጋሉፕ አናሊቲክስ የተሰኘውና በአለም አቀፍ ህግና ስርኦቶች መከበር ዙሪያ የሚሰራው ተቋም በ 141 የአለማችን ሃገራት ላይ በተካሄደው ጥናት ኢትዮጵያ 42ኛ ደረጃ ላይ መገኘቷን አስታውቋል።

በየሃገራቱ ያሉ ዜጎች በፖሊስ ላይ ያላቸውን መተማመንና በ 141ዱ ሃገራት የሚገኝን የስርቆት ደረጃ መለኪያነት በተወሰዱበት በዚሁ አለም አቀፍ ጥናት፣ ሲንጋፖር፣ ኡዝቤኪስታንና፣ ሆንግ ኮንግ የተረጋጉ ተብለው ከ አንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ማግኘት ችለዋል።

በሶስቱ ሃገራት የሚገኙ ሰዎች በፖሊስ ላይ ያላቸው መተማመን ከፍተኛ ሲሆን በምሽትም ያለምንም ፍርሃት እንደሚንቀሳቀሱ በረፖርቱ ላይ ተመልክቷል።

ዛሬ ረቡዕ ይፋ በተደረገው በዚሁ ረፖርት ስርቆት የተለመደበት ነው የተባለው ደቡብ አፍሪካ በ 138ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፣ የህግ አስከባሪዎቿ በሙስና የሚታሙባት ኬንያ ደግሞ 118ኛ ሆና መገኘቷን ዘስታር የተሰኘው የኬንያ ጋዜጣ ዘግቧል። ግብፅ በ31ኛ ደረጃ ላይ የተፈረጀት ሲሆን ኒጀር ደግሞ በ41ኛነትን ደረጃ ይዛለችን።

ከ20 አመት በላይ በጦርነት ውስት የምትገኘው ጎረቤት ሶማሊያ 72ኛ ደረጃ ስታገኝ፣ አዲሲቷ ሃገር ደቡብ ሱዳን በ 136ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለችን።

ከአለም በ 21ኛ ደረጃ ላይ የተፈረጀችው ሩዋንዳ ደግሞ ከ አፍሪካ ደህንነቷ አስተማማኝ ተብሎ ሰላማዊ አገር ተብላ ተመርጣለች።

በሃገራት ውስጥ ያለ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ህዝቦች በፅጥታ ሃይሎች ላይ ያላቸው እምነት ማነስ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ጋሉፕ አናሊቲክስ በመታዊ ረፖርቱ አመልክቷል።