ኢትዮጵያ በተፈጸሙ ግድያዎችንና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንድታጣራ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

ሰኔ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ባለፉት ጥቂት ወራት በተቃዋሚ መሪዎች ላይ የተፈጸመው ግድያና በመላ አገሪቱ በተቃዋሚ ድርጅት አባላት ላይ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ረገጣ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ ላይ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው ብሏል።
የአፍሪካ ህብረትና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን መርምረው ሪፖርት አለማድረጋቸውንም ድርጅቱ ወቅሷል። ምርጫው እስከሚካሄድበት ጊዜ ድረስ ከ500 በላይ የመድረክ አባላት መታሰራቸውን የገለጸው አምነስቲ፣ 46 ሰዎች ሲደበደቡ፣ 6 የሚሆኑት ደግሞ በጥይት ቆስለዋል፣ 2 አባሎችም ተገድለዋል።የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል የሆነው ግዲላ ጨመዳ በምእራብ ሸዋ ዞን በዲማ ቀጌ ወረዳ በፖሊስ መገደሉንም አምነስቲ ጠቅሷል። የ27 አመቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሳሙኤል አወቀ በደብረማርቆስ ከተማ መገደሉን፣ የሰማያዊ አመራሮች ግድያው ፖለቲካዊ መሆኑን መግለጻቸውንም በሪፖርቱ አመልክቷል። የአረና ፓርቲ አባል የሆኑት የ48 አመት ጎልማሳው አቶ ታደሰ አብርሃም ሶስት ሰዎች ሊያንቋቸው ሲሞክሩ ታግለው ማምለጣቸውን ይሁንና ትንሹ ቆይተው ቤት እንደደረሱ መሞታቸውን ድርጅቱ ጠቅሷል።
ሰኔ 11 ደግሞ የመድረክ አባል የሆነው ብርሃኑ ኢራቡ በፖሊስ በተያዘ በ24 ሰአታት ውስጥ ሃድያ ዞን ሶሮ ወረዳ በሚገኝ ወንዝ አካባቢ ተገድሎ መገኘቱን አምነስቲ ጠቅሷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፍትህ ሚኒስቴር፣ ፌደራል ፖሊስና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ምርመራ አድርገው ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቅረቡ ጠይቋል።
የሂውማን ራይትስ ወቹ ፌሊክስ ሆርን በጻፈው ጽሁፍ ደግሞ ገዢው ፓርቲ የአፈናውን ዘር ቀድም ብሎ መዝራቱን ገልጿል። በ2002ቱ ምርጫ ኢህአዴግ 99.6 % የፓርላማ ወንበሮችን አሸንፊያለው ባለበት ማግስት የፖለቲካ ምኅዳሩን መዘጋቱን የገለጸው ፊሊክስ፣ ነፃ የመገናኛ ብዙሃን እንዲከስሙ መደረጋቸውን ፣የሲቪክ ማኅበራት ጭራሽኑ መጥፋታቸውንና ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች መከልከላቸውን ጠቅሷል።
“የተቃዋሚ መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው፣ መራጮቻቸውን ጨምሮ የሽብርተኝነት ክስ በመክሰስ ወሕኒ ቤት ያጉሯቸዋል።የተቃዋሚ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ለማስመዝገብና ገቢ ለማሰባሰብ በህጋዊነት እንዳይንቀሳቀሱ ክትትል ይደረግባቸዋል።የደኅንነት ኃይሎች በሕዝባዊ ሰልፍ ላይ ያሉ ግለሰቦችን በመከታተል ያስጨንቃሉ፣ያፍናሉ፣ንብረቶቻቸውን ይቀማሉ፣ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ ፍቃድ ይከለክሉዋቸዋል። ባለፉት ሁለት ስምንታት ውስጥ ብቻ ብዛት ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና እጩ ተወዳዳሪዎች በድብደባ ለሞት ተዳርገዋል።ቀሪዎቹ ደግሞ በአስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።” ሲል ፊሊክስ ጽፏል።
ሁለቱ የኢትዮጵያ ቁልፍ ደጋፊዎች የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን የፖለቲካ አፈና በዝምታ እያዩት ነው ያለው ፊሊክስ፣ እንዲያውም ኢትዮጵያዊያኑ ሰላማዊ ምርጫ በማድረጋቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋቸዋል ብሏል።እነሱን ያስጨነቃቸው ፍትሃዊ ምርጫ መካሄዱ ሳይሆን ካለ ብጥብጥ መጠናቀቁ ነው ያለው ፊሊክስ፣ “ይህ መጭውን ጊዜ አርቆ ካለማሰብ የሚመጣ ውሳኔ አደገኛ ነው፤ ባለስልጣናቱ የረዥም ጊዜ ዘላቂ መረጋጋትን የሚሹ ከሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በቅርበት መከታተል ይገባቸዋል።” ሲል መክሯል።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይሆናል ብሎ የገመተው ነው የሆነው የሚለው ፊልክስ ፣ በመጨረሻም መቼ ይሆን የኢትዮጵያ አገሮች አይኖቻቸውን የሚከፍቱት ሲል ጠይቋል።