ኢሳት (ታህሳስ 7 ፥2009)
ኢትዮጵያ በጎረቤት ሶማሊያ በተናጠል አሰማርታ የምትገኘውን ቀሪ ሰራዊቷን በቀጣዩ ወር አጠቃልላ እንደምታስወጣ ተገለጸ።
በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ እየተካሄደ ያለውን ምርጫ ለማገዝ በሚል ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ መደረጉን ፍራንስ 24 የተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማደረግ ዘግቧል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከታህሳስ ወር 2006 አም ጀምሮ ቁጥሩ ያልተገለጸ ሰራዊት በሶማሊያ አሰማርታ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደሮቿን ሳታስወጣ መቆየቷ ይታወሳል።
በእስካሁኑ ሂደት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ከደቡባዊ እና ከማዕከላዊ ሶማሊያ ጠቅልለው ወጥተዋል። ወደ 600 የሚጠጉ ሰላም እስከባሪ ወታደሮች አሁንም ድረስ በሃገሪቱ እንደሚገኙ የቴሌቪዥን ጣቢያው በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።
በተያዘው ወር መጨረሻ በሶማሊያ የሚካሄደውን ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ተከትሎ እነዚሁ ቀሪ ወታደሮች ከሶማሊያ ለቀው እንደሚወጡ ታውቋል።
ስማቸው ያልተገለጸ የቀጠናው የጸጥታና ደህንነት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ በሶማሊያ በተናጠል አሰማርታ ለምትገኘው ሰራዊት በቂ ድጋፍ ከምዕራባዊያን ዘንድ አለማግኘቷ ቅሬታ እንዳሳደረባት አስረድተዋል። የመከላከያ ኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ሃገራቸው በተናጠል ላሰማራችው ሰራዊት ወጪን መሸፈን ወደማትችልበት ሁኔታ ውስጥ መግባቷን በተደጋጋሚ ሲገልፁ እንደነበር ፍራንስ 24 በዘገባው አውስቷል።
ይሁንና ምዕራባውያን ሃገራትና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በአፍሪካ ህብረት ስር ተሰማርቶ ከሚገኘው የሰላም አስከባሪ ሃይል ውጭ ተጨማሪ ገንዘብ ለመመደብ ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያው ገልጿል።
ጉዳዩን አስመልክቶ በኢትዮጵያና በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ይፋዊ ምክክር ይካሄድ አይካሄድ የታወቀ ነገር የሌም። የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በቂ ድጋፍና ትኩረት አለመስጠታቸው ወታደሮቿን ለማስወጣት ከምክንያቶቹ መካከል አንዱ መሆኑን ሲገልፅ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ያጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረትና በሃገረቱ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ አመጽ ሰራዊቷ በሶማሊያ እንዲቆይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም የፖለቲካ ተንታኞች ለፍራንስ 24 ጣቢያ አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስካባሪ ሃይል በሶማሊያ ከተሰማራ ከሰባት አመት በፊት ጀምሮ ወደ 2ሺ የሚጠጉ ወታደሮች ተገድለዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ወታደሮችን ያዋጡ ሃገራት ቁጥሩን ይፋ ከማድረግ ተቆጠበዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና የደህንነት ባለሙያ ፖል ዊሊያምስ የኢትዮጵያ ሰራዊት በአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ ውጤታማ ድሎችን ቢቀናጅም ሰራዊቱ በሶማሊያውያን ዘንድ ድጋፍ የሌለው መሆኑን ለቴሌቪዥን ጣቢያው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በሶማልያ የሚገኘው ወደ 22 ሺ አካባቢ የአፍሪካ ሰላም አስካባሪ ሃይል ተጨማሪ ወታደሮች እንዲቀላቀሉት ቢደረገም የሚፈለገው ሰላምና መረጋጋት በሶማሊያ ሊመጣ እንደማይችል የፖለቲካ ባለሙያዎች አስረድተዋል። ይሁንና የሶማሊያ ወታደሮችና ፖሊሶችን አቅም ማጎልበት ለችግሩ ብቸኛ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።