ኢሳት (ሚያዚያ 6 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ በሰው ሃብት ልማት ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት መካከል ዝቅተኛ አፈጻጸም ላይ እንደምትገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ይፋ አደረገ።
የ2016 አም አመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው ድርጅቱ ኢትዮጵያ ከ189 ሃገራት በሰው ሃብት ልማቱ በ174ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንና የያዘችው ደረጃም በአህጉሪቱ ዝቅተኛው መሆኑን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ጥናቱን ካካሄደባቸው 189 ሃገራት መካከል 41ዱ ዝቅተኛ የተባለው የሰው ሃብት ልማት ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን፣ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያም ከእነዚሁ ሃገራት ተርታ ተመድባለች።
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት፣ የማህበረሰብ የጤና አጠባበቅ፣ የማህበረሰብ ጥበቃ እንዲሁም ጾታዊ እኩልነት በሰው ሃብት ልማቱ በመስፈርትነት መቀመጣቸውን መረዳት ተችሏል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ የሆኑት አሁና አኖቺ ሃገሪቱ ላለፉት በርካታ አመታት የሰው ሃብት ልማቷን ለማሻሻል ጥረት ስታደርግ ብትቆይም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መቀጠሏን ገልጸዋል።
ሃገራት ለዜጎቻቸው የመሰረታዊ አገልግሎትን ማዳረስና ማስፋፋት እንደሚኖርባቸው ያሳሰበው ድርጅቱ፣ የበሽታዎች ስርጭትን መከላከል ግጭትን ማስወገድና ሙስናን መቆጣጠር ለሰው ሃብት ልማት መጎልበት ወሳኝ መሆኑን አመልክቷል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛ አፈጻጸምን ያስመዘገቡት 41ዱ ሃገራት በነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረትን ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ አሳስቧል።
ኢትዮጵያ ላለፉት 10 አመታት ባለሁለት አህዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን ስትገልፅ ብትቆይም እድገቱ በሰው ሃብት ልማት ላይ ያመጣው ለውጥና ውጤት የማይመጣጠን መሆኑም ተመልክቷል።
ጎረቤት ኬንያ፣ ኔፓል፣ እና ፓኪስታን ባለፉት አመታት የነበራቸውን የሰው ሃብት ልማት በማሻሻል ከዝቅተኛ ወደ መካከለኛ ደረጃ ተሸጋግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ፈረንጅቹ አቆጣጠር በ2005 አም የማህበረሰብ ጥበቃ ፕሮግራም ተግባራዊ ቢያደርግም የድርቅ አደጋ በአሁኑ ሰዓት ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ለምግብ እጥረት ዳርጎ እንደሚገኝ በዋቢነት ቀርቧል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አብዛኛው ህዝባቸው በድህነት ውስጥ የሚገኙ ሃገራት የዜጎቻቸውን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎችን ካላካሄዱ በሰው ሃብት ልማት ዘንድ መሻሻል እንደሚጠበቅ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ኖርዌይ፣ አውስትራሊያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ዴንማርክ ሲንጋፖር፣ ኔዘርላንድ፣ አየርላንድ፣ አይስላንድ፣ እና ካናዳ በአለም ካሉ ሃገራት መካከል በሰው ሃብት ልማታቸው የተሻሉ ተብለው ከአንደኛ እስከ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
እነዚሁ ሃገራት ለዜጎቻቸው ትምህርትን ጨምሮ የተለያዩ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በማደራስ በምሳሌነት የተቀመጡ ሲሆን፣ የዜጎቻቸው በእድሜ የመቆየት ጣሪያ የተሻለ እንደሆነ በሪፖርቱ ተብራርቷል።