ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች ተባለ

ኢሳት (ሃምሌ 26 ፥ 2008)

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት መስቀለኛ መንገድ ላይ እንደምትገኝ በአሜሪካ አገር ሞርጋን ስቴት ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ ገለጹ። Dr. Getachew Metaferia

ከቪኦኤ እንግሊዝኛው አገልግሎት ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉን ያማከለ ግልፅና እውነተኛ ምርጫ ካላደረገ፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ህልውና ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይወድቃል ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ገለጻ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያና ጎንደር የተደረጉት ተቃውሞዎች መንስዔ በከፊል በጎሳ ላይ የተመሰረተው ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግራይ በሚል የከፋፈለው ፌዴራሊዝም ፖሊሲ ነው።  ሌላው የግጭቱ መንስዔ የትግራይ ክልል ወደጎንደር በመስፋፋት ከወልቃይት ጠገዴ መሬት መውሰዱ እንደሆነ የተናገሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ፣ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ አማራ እንጂ ትግሬ አይደለንም እያለ ባለበት ሁኔታ፣ የትግራይ መንግስት ግን በግድ ትግሬ ናችሁ በማለት ወደትግራይ መከለሉ ለግጭቱ መንስዔ ሆኗል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚታየው የዲሞክራሲ ዕጦት ለህዝባዊ ተቃውሞ አስተዋጽዖ እንዳደረገ የተናገሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ የመናገር ነጻነት፣ የፕሬስ ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ህዝባዊ ተቃውሞ እንደሚኖር ግልጽ አድርገዋል። በአገሪቷ ውስጥ የተንሰራፋው ድህነት፣ እና የጥቂት ሰዎች መበልጸግ አብዛኛውን ህዝብ ለተቃውሞ እንዲነሳሳ ማድረጉም አመልክተዋል።

በጉልበት ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ኢትዮጵያን ለችግር ዳርጓታል ያሉት ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ፣ መንግስት የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሰውን ካልቀየረና ሁሉን የሚያሳትፍ መንግስት ካላቋቋመ የአገሪቷ ህልውና አደጋ ውስጥ እንደሚሆን ለአሜሪካ ድምጽ የእንግሊዝኛው አገልግሎት ተናግረዋል።

100 ፐርሰንት የፓርላማ ወንበር አሸንፊያለሁ ከሚል መንግስት ምን ትጠብቃለህ ያሉት ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በታሰሩበት ሁኔታ ሰላም አይኖርም፣ ሊኖርም አይችልም ብለዋል።

የውጭ መንግስታትም የኢትዮጵያ መንግስት ለተቃዋምዎች በር እንዲከፍትና ነጻ ምርጫ እንዲያደርጉ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።