ኢሳት (ጥር 19 ፥ 2008)
ኢትዮፕያ በአለማችን ሙስና ይካሄድባቸዋል ተብለው ከተጠኑ 168 ሃገራት መካከል 103ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን በጉዳዩ ዙሪያ ጥናትን ያካሄደው ትራስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሃሙስ ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታወቀ።
ሃገሪቱም ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ ይፈጸምባቸዋል ተብለው በቀይ ቀለም ከተቀመጡት ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗንም ሪፖርቱ አመልክቷል።
አውሮፓዊቷ ዴንማርክ በአለማችን ሙስና በጣም አነስተኛ ሁኔታ የሚፈፀምባት ሃገር ተብላ በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠች ሲሆን ሶማሊያና ሰሜን ኮሪያ ከ 100 ነጥብ ስምነት ብቻ በማግኘት የመጨረሻዎቹ ሃገራት ሆነዋል።
በባለስልጣናት የሚፈጸሙ ሙስናዎችና ባለስልጣናት በመንግስት ያላቸው ተጠያቂነት በመስፈርትነት በተካተቱበት በዚሁ ጥናት ዶሚንካን ሪፐብሊክ፣ ኮሶቮና፣ ሞልዶቢያ፣ ከኢትዮጵያ ጋር እኩል 103ኛ ደረጃን አግኝተዋል።
ሶስቱ ሃገራት ሙስና በአለማችን ከሚፈጸምባቸው ዋነኛ ሃገራት መካከል የሚገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም በ2015ቱ ጠቋሚ ሪፖርት ከሃገራቱ ተርታ መመደቧን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።
ፊንላንድ፣ ስዊድን፣ ኒውዚላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይና ስዊዘርላንድ ከ2ኛ እስከ 7ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
አሜሪካ በ2014 የነበራትን ደረጃ በማሻሻል 16ኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን፣ ሁለቱ ሱዳኖች እና አንጎላ ከ163 እስከ 165 ባለው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የባለፈው አመት ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሙስና አሁንም ድረስ የአለማችን ዋነኛ የልማት ችግር ሆኖ እንደሚገኝ ገልጿል።
በጥናቱ ከታቀፉት 168 ሃገራት መካከልም 64ቱ ብቻ ደረጃቸውን ያሻሻሉ ሲሆን 53ቱ ደግሞ ከደረጃቸው ዝቅ ብለው መገኘታቸውን ከድርጅቱ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
የመንግስት ባለስልጣናት የሚዘርፏቸው ገንዘቦች እንዲሁም ያለ-ግልፅ ጨረታ የሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጄክቶች ለሙስና አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉም ተመልክቷል።