ኢሳት (የካቲት 16 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች 2016 አም በአለም መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከተፈጸሙባቸው ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርት ገለጸ።
በሃገሪቱ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ለአንድ አመት ያህል ጊዜ የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተስተናገዱበት ወቅት ሆኖ መመዝገቡን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የ2016 አም ሪፖርቱን አስመልክቶ ባወጣው የሰብዓዊ መብት ቅኝቱ አስፍሯል።
በዚሁ በኦሮሚያ ክልል የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በሰላማዊ ሰልፎች ላይ ቀጥተኛ የጥይት ተኩስ ዕርምጃ ሲወስዱ እንደነበር ያወሳው ድርጅቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው ሊያልፍ መቻሉን ገልጿል።
ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ከጥቂት አመታት በፊት ተግባራዊ ያደረገውን የሽብርተኛ ወንጀል ህግ የሃገሪቱ ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጡ ማነቆ ሆኖ መቀጠሉን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አመልክቷል።
በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መጠነ ሰፊ ግድያ ከተፈጸመባቸው ሰዎች በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙና በሃገሪቱ በመፈጸም ላይ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመሻሻል ይልቅ መባባስ ማሳየቱን አክሎ አመልክቷል።
በ159 የአለማችን ሃገራት ላይ ያካሄደውን የሰብዓዊ መብት ጥናቱን አስመልክቶ ባለ 408 ገፅ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በዜጎቿ ላይ ከወሰደችው የሃይል ዕርምጃ በተጨማሪ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ አፈና መፈጸሟንም በሪፖርቱ አስነብቧል።
በአፍሪካ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ቻድ፣ ጋቦን፣ ጋምቢያ፣ ዩጋንዳ፣ እና ሌሴቶ ተመሳሳይ የኢንተርኔት አፈና ሲፈፅሙ መቆየታቸውን ያወሳው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ባለፈው የፈረንጆች አመት በአለም ዙሪያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ መሻሻል አለማስመዝገቡንም አክሎ ገልጿል።
መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አካሄዳለች ከተባለችው ኢትዮጵያ ጎን ለጎን ግብፅ፣ ባህሬን፣ ፊሊፒንስና ቱርክ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸውን መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገው አለም አቀፍ ተቋም አስታውቀዋል።
23 ሃገራት የጦር ወንጀል የተፈጸመባቸው ሲሆን፣ 22 የአለማችን ሃገራት ደግሞ መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ በጠየቁ ዜጎቻቸው ላይ ግድያ መፈጸማቸውን ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።
በኢትዮጵያ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ የሰብዓዊ መብጥ ጥሰቶች ምክንያት ሆኖ መቀጠሉንም አምነስቲ ኢንተርናሽናል አክሎ ገልጿል።
የአሜሪካ፣ የሃንጋሪ፣ የቱርክ እና የፊሊፒንስ አመራሮች በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው የሰላ ትችት ቀርቦባቸዋል።