ኢሳት (መስከረም 10 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በአባይ ግድብ ግንባታ ላይ ይግባኝ የማይኖረው ጥናት እንዲጀመር ማክሰኞ በሱዳን መዲና ካርቱም የመጨረሻ ስምምነት ደረሱ።
ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች በቀጣዮቹ 11 ወራቶች ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ በማጥናት ሪፖርታቸውን ለሶስቱ ሃገራት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አርቴሊያና BRL የተሰኙት ኩባንያዎች የሚያካሄዱ ጥናት ይግባኝ የማይኖረው ሲሆን፣ ሃገሮቹ ለጥናቱ ውጤት ተገዢ እንደሚሆኑ በተደረሰው ስምምነት መጠቀሱን አል አህራም የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
በጥናቱ ሂደት በሃገሪቱ የሚነሱ ህጋዊ ጉዳዮች ለመከታተል አንድ የብሪታኒያ የህግ ተቋም መካተቱንና የተፈረመው ስምምነት የተለያዩ አንቀጾችን የያዘ 200 ገጽ መያዙ ታውቋል።
ይሁንና የመንግስት ባለስልጣናት ለአራት አመታት ያህል በግድቡ ግንባታ ላይ ምንም አይነት ማሻሻያ አይደረግም፣ ግንባታውም በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ የለም ሲሉ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው።
በሱዳን የተደረሰው ስምምነት ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ እንዲደረግ ፕሮግራም ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ መንግስት የጸጥታ ችግር አለብኝ በሚል ፕሮግራሙ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል።
የተደረሰውን ስምምነት “ታሪካዊ” ነው ሲሉ የገለጹት የግብፁ ውሃና መስኖ ሚኒስትር ሞሃመድ አብደል አቲ ሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ላይ የሚያመጣውን አካባቢያዊ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በስፋት እንደሚዳስስ ለመገኛኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ማክሰኞ በሱዳን ካርቱም ከተደረሰው ስምምነት አስቀድሞ የኢትዮጵያ መንግስት በግድቡ ግንባታ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ካስፈለገ ጉዳዩ ሊታይ እንደሚችል ለግብፅ ፍንጭ መስጠቱ ይታወሳል።
በሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎች የሚከናወነው የባለሙያዎች ጥናት በግብፅና በሱዳን ባሉ የሃይል ማመንጫ ተቋማት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዲጠና በስምምነቱ መቀመጡን የግብፅ መስኖ ሚኒስቴር ለሃገራቸው መገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል።
ሶስቱ ሃገራት ለሁለቱ ኩባንያዎች የሚከፈለውን ወደ አምስት ሚሊዮን ዩሮ (ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ) በጋራ አንደሚሸፍኑትም ለመረዳት ተችሏል።
በካርቱም የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ ከኢትዮጵያ በኩል የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።