ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የአባይ ግድብን ተጽዕኖ የሚያጠኑ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ሊፈራረሙ ነው

ኢሳት (ነሃሴ 26 ፥ 2008)

በመገንባት ላይ ባለው የአባይ ግድብ ዙሪያ ላለፉት አራት አመታት ሲወዛገቡ የቆዩት ግብፅ፣ ኢትዮጵያና፣ ሱዳን፣ የአባይን ግድብ ተፅዕኖ እንዲያጠኑ ከተመረጡ ሁለት የፈረንሳይ አማካሪ ኩባንያዎች ጋር በሚቀጥለው ሳምንት የስምምነት ሰነድ እንደሚፈራረሙ ተገለጸ።

የስራ ውል ስምምነት የሚፈራረሙት የሶስቱም አገራት የውሃ ልማት ሚኒትሮች ሲሆኑ፣ አርቴሊያና (Artelia) ቢአር ኤል (BRL) የተባሉ ኩባንያዎች የግድቡን ይዘትና፣ ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ሊያመጣ የሚችለውን ቴክኒካዊ ጥናት በጥልቅ አጥንተው እንደሚያቀርቡ ታውቋል።

የስምምነት ፊርማው በካርቱም ነሃሴ 30 እና ጳጉሜ 1 2008 እንደሚፈረም ያስታወቁት አንድ የግብፅ ባለስልጣን፣  ኢትዮጵያ ስምምነቱ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ እንደምትፈልግ አል አህራም የተባለ የግብፅ ጋዜጣ ዘግቧል። ኢትዮጵያ ስምምነቱን ለምን እንዲራዘም እንደፈለገች ባይታወቅም፣ አሁን በአገሪቷ እየተቀጣጠለ ያለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ቀውስ ወደከፋ ደረጃ እንዳይደርስ ሰግታ ሊሆን እንደሚችል እሳት ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች አስረድተዋል።

በአባይ ግድብ ዙሪያ ሲወዛገቡ የነበሩት ግብፅና ኢትዮጵያ፣ ግብጽ ባቀረበችው የትብብር ሰነድ ላይ ስምምነታቸውን መግለጻቸውን የግብፅና የሱዳን መገናኛ ብዙሃን ባለፈው እሁድ መዘገባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት አራት አመታት ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ስለማይኖር ምንም አይነት ማስተካከያ አይደረግበትም ሲል አቋሙን ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል።

ሆኖም ግብጽና ኢትዮጵያ ስምምነት ላይ ሊደርሱ ባለመቻላቸው አርቴሊያና (Artelia) ቢአር ኤል (BRL) የተባሉ ኩባንያዎች የግድቡን ይዘትና ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚያመጣው ተጽዕኖ በሚያቀርቡት ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ ማስተካከያ አደርጋለሁ በማለት ለግብፅ መንግስት የማረጋገጫ ፍንጭ መስጠቷ ይታወሳል።

ይህንኑ ተከትሎ በግድቡ ላይ ማብራሪያን የሰጡት ፕሬዚደንት አል-ሲሲ ሃገራቸው የነበራት ስጋት እየቀነሰ መምጣቱን ለህዝባቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።

ሁለቱ ኩባንያዎች ይፋ የሚያደርጉት የጥናት ውጤት ይግባኝ የሌለው እንዲሆን ከዚህ በፊት በካርቱም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።