ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲባረሩ ተወሰነ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 17/2010)

ማላዊ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ 22 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲባረሩ ተወሰነ።

ኢትዮጵያውያኑ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ከሀገር እንዲባረሩ የተወሰነው ጉዳያቸውን በተመለከተ የሚያግዛቸው አስተርጓሚ በመጥፋቱ እንደሆነም ተመልክቷል።

በሌላ ዜና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ 5 ኢትዮጵያውያን በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን አፍሪካ ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል።

ማላዊ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ገብታችኋል በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉት 22 ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የማላዊው ጋዜጣ ናይሳ ታይምስ በዘገባው አስፍሯል።

ኢትዮጵያውያኑ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ክሳቸውን መረዳት ባለመቻላቸውና አስተርጓሚም በመጥፋቱ ዳኛው ይባረሩ የሚለውን ውሳኔ ማሳለፋቸው ታውቋል።

የማላዊ መንግስት ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጭምር አስተርጓሚ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለትም ታውቋል።

የማላዊ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደተናገሩት ኢትዮጵያውያኑን በማላዊ ለማቆየት ተጨማሪ ወጪ ያስፈልጋል።

ስደተኞቹን ለመመገብም የማላዊ መንግስት ገንዘብ ለማውጣት ይገደዳል። ከዚህ ሁሉ ፋይሉን ዘግቶ ሰዎቹን ማባረሩ ተመራጭ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህም 22 ኢትዮጵያውያን እንዲባረሩ ተወስኗል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ 5 ኢትዮጵያውያን በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን አፍሪካ ኒውስ ኤጀንሲ በዘገባው አመልክቷል።

ያሽከረክሩት የነበረው መኪና ከሌላ መኪና ጋር በመጋጨቱ አራቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ አንደኛው ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል።

አፍሪካ ኒውስ ኤጀንሲ በዘገባው እንዳመለከተው ከሳምንት በፊት ደረሰ የተባለው ይህ አደጋ የተከሰተው በደቡብ አፍሪካ ከዴላ ራቪል ወደ ቪረበርግ ሲጓዙ የነበሩት ኢትዮጵያውያን በናሚቢያውያን ከሚሽከረከር ሌላ መኪና ጋር በመጋጨታቸው ነው።

ከናምቢያውያኑ ወገን በአደጋው የሞተ ባይኖርም ሶስቱም በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት በሆስፒታል ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ከዘገባው መረዳት ተችሏል።

ምርመራው በቀጠለው በዚህ አደጋ የሞቱት አምስቱ ኢትዮጵያውን እድሜያቸው ከ31 እስከ 54 አመት እንደሆነም የደቡብ አፍሪካ የሰሜን ምዕራብ የደህንነትና ትራንስፖርት ሃላፊ ገልጸዋል።

በአደጋው ላለቁት ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝተዋል።