ኢትዮጵያውያን በጋራ መታገል እንዳለባቸው ዶ/ር በያን አሰቦ ገለጹ

ኢሳት (ህዳር 27 ፣ 2008)

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር በያን አሶባ፣  ዜጎች በአንድነት ተባብረው የህዝቦችን የነጻነት ፍላጎት ከዳር እንዲያደርሱ ለመላው ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቅርበዋል።

ቀድሞ የኦነግ የአመራር አባል የነበሩት ዶ/ር በያን፣ የአገሪቷ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በመላው ኢትዮጵያ በሁሉም ማዕዘናት የነጻነት እንቅስቃሴያቸውን በጋራ ማካሄድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ተነጣጥሎ የሚደረግ አመጽና እምቢተኝነት በምንም መልኩ ሊሳካ እንደማይችል፣ ህዝቡ በጋራ ለነጻነትና ለፍትህ ጥያቄዎች አብሮ መታገል እንዳለበት ለኢሳት ገልጸዋል።

ሆኖም፣ የወያኔ አገዛዝ የራሱን ወኪሎች በህዝቡ ውስጥ በማስገባት ህዝብን ከህዝብ በተለይም አማራንና ኦሮሞን በማጋጨት ለስልጣን ማራዘሚያነት ሊጠቀም እንደሚችል፣ ህዝቡ ከእንደዚህ አይነት ጥፋት ራሱን ማራቅ እንዳለበት ዶ/ር በያን መክረዋል።

በግብታዊነት የተነሳውን የ 1966 አብዮት ያስታወሱት ዶ/ር በያን፣ አሁን በኦሮሚያ የተነሳው አመጽ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ሊቀይር ይችላል ብለዋል። የህዝቦቹ የወደፊት እድል የተያያዘ በመሆኑ አንዱ ለአንዱ አብሮ መቆም እንዳአለባቸው አስገንዝበዋል።

በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የተጀመረ ተቃውሞ፣ ባለፉት 24 ዓመታት ሲደርስ የነበረውን የእኩልነትና የዴሞክራሲ እጦት፣ የውሸት ፌዴሬሽንና የህዝቦችን ጭቆና ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ክስተት ነው በማለት አክለዋል። የማስተር ፕላኑ ተቃውሞ የመጣው ይህ መንግስት በ100 ፐርሰንት ተመርጫለሁ ባለበት ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑ፣ በውሸት ላይ የተመሰረ መንግስት መሆኑን ዶ/ር በያን ለኢሳት ገልጸዋል።

እየተደረገ ያለው ተቃውሞ ህወሃት/ኢሕአዴግ ባወጣው ህገመንግስት የህዝቡ መሰረታዊ መብት መሆኑን ልብ ማለት እንደሚገባ የገለጹት ዶ/ር በያን፣ ስልጣን ላይ ያለው ሃይል ግን የራሱን ህግ እንኳን ባለማክበር በዜጎች ላይ እስር፣ እንግልት፣ ድብደባና፣ ግድያ በመፈጸም የተመሰከረለት አምባገነን መሆኑን አብራርተዋል።

ጥቂት የህወሃት ባለስልጣናት የሚበለጽጉበት አካሄድ በቃ መባል ይገባዋል ያሉት ዶ/ር በያን፣  ኦህዴድን ተቀጽላ ሳይሆን ከህዝቡ ጋር በመሆን ትክክለኛ ፌዴሬሽን እንዲሰፍን መታገል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉልና፣ ደቡብ ህዝቦች በተደረጉ የመሬት ሽሚያዎች፣  በጎንደር ለሱዳን የተሰጠው መሬትን በማስመልከት ከአካባቢው ህዝብ ውጭ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ አለመቃወሙ ስህተት እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር በያን አሶባ፣ ይህም የአገዛዙን የከፈፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሰለባ መሆናችንን ያሳየ ክስተት  ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ከአመት በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ በአመጹ እስካሁን ከ 60 ሰላማዊ ሰዎች በላይ ተገለዋል። ተቃውሞ አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል።