ኢትዮጵያውያን በገፍ ወደ የመን እየተሰደዱ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ

ኢሳት (ጥር 11 ፥ 2008)

ከ80ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በጦርነት እልባት ወደላገኘባት የመን መሰደዳቸውንና የኢትዮጵያውያኑ የየመን ስደት እሳስቦት እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረቡዕ ይፋ አደረገ።

በየመን የተቀሰቀሰው ጦርነት ቀጥሎ ቢገኝም ባለፈው የፈረንጆች አመት ብቻ 82 ሺ 268 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ህይወታቸውን ለአደጋ በሚጥል ጉዞ ወደየመን መግባታቸው ድርጅቱ ገልጿል።

ስደተኞቹ በጀልባዎች የሚያደርጉትም ጉዞ ሆነ የመን ከገቡ በኋላ የሚያጋጥማቸው ችግር እጅግ አስከፊ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል-አቀባይ የሆኑት አድሪያን ኤድዋርድ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አስታውቀዋል።

ከኢትዮጵያውያኑ ቀጥሎ ከ 10ሺ የሚበልጡ ሶማሊያውያን በሃገራቸው ያለን ግጭት በመሸሽ ወደየመን እንደገቡና በአጠቃላይ 95 ስደተኞች በጀልባ አደጋ ህይወታቸው ማለፉን ቃለአቀባዩ ገልጸዋል።

ይሁንና ከሟቾቹ መካከል ምን ያህሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሆኑ የተገለፀ ነገር የሌለ ሲሆን የኢትዮጵያውያኑ የየመን ስደት አሁንም ድረስ ቀጥሎ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያውያኑና የሶማሊያውያኑ የየመን ጉዞ እንቆቅልሽ ሆኖብናል ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ስደተኞች ህይወታቸውን አደጋ ላይ በጣለ አካሄድ ለምን ወደጦርነት ቀጠና እንደሚጓዙ ግራ የሚያጋባ ነው ሲሉም የድርጊቱን አሳሳቢነት ገልጸዋል።

በተለይ የኢትዮጵያውያኑ ዛሬም ድረስ በመጠን ጨምሮ መቀጠሉ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖብናል በማለት ሃላፊው ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አስረድተዋል።

በቅርቡም በሶማሊላንድ በኩል ወደ የመን ሲጓዙ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በጀልባ ላይ በደረሰ አደጋ መሞታቸው ይታወሳል።

ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን በጎረቤት ሃገራት በኩል የመንን ጨምሮ ወደተለያዩ የአውሮፓና የአረብ አገራት መሰደዳቸውንና ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻሉትም ህይወታቸው በማለፉ የዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት  መረጃ (IOM) ያመለክታል።