ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 23/2010)

በሊቢያ ከ400 በላይ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ።

አማጽያኑ በሚቆጣጠሩት ግዛት በስደት የገቡ ኢትዮጵያውያን በአንድ መጋዘን ውስጥ ታጭቀው በስቃይ ውስጥ እንደሚገኙም ታውቋል።

በቅርቡ ብቻ 5 ኢትዮጵያውያን በድብደባና በበሽታ መሞታቸውንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ፋይል

የኢትዮጵያ መንግስት እንዲደርስልን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም ሲሉ በችግር ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን ለኢሳት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያኑ ወገን ይድረስልን ሲሉም ጥሪ አድርገዋል።

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሊቢያ የገቡት ሀገር ቤት የህዝብ ንቅናቄ በተከሰተ ሰሞን ነው።

በተለይም ከኦሮሚያ፣ ከአማራና ከአዲስ አበባ አካባቢዎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ሀገር ጥለው ወጥተዋል።

በሱዳን አቋርጠው መዳረሻቸው አውሮፓ እንዲሆን አልመው፡ ሊቢያ ሲደርሱ የገጠማቸው ግን የሸሹትና ከሀገር ያስወጣቸው ስቃይና መከራ ሆኗል።

ከሊቢያ መውጣት አልቻሉም። ወደኋላ መመለስም የሚሞከር አልሆነም።

በመጋዘን ውስጥ ታጭቀው ከአንድ ዓመት በላይ የሆናቸው ከ2500 በላይ ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያንና የሌሎች ሀገራት ዜጎች አሁን ያሉበት ሁኔታ አደገኛ መሆኑን ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ከ400 በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው።

በቅርቡ በአንድ ቦታ በሚገኘው መጋዘን ውስጥ ከታጨቁት መካከል 15 የሚሆኑት ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከእነዚህም 5ቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ታውቋል።

በሊቢያ ወንድሟ በጠና የታመመባት ኢትዮጵያዊት ከጎንደር ደውላ ለወንድሜ ድረሱለት ስትል የተማጽኖ ጥሪ አቅርባለች።

በኢትዮጵያውያኑ ላይ የሚደርስባቸው ስቃይ ተዘርዝሮ አያልቅም። ምግብ በሳምንት አንድ ቀን የሚቀርብላቸ መሆኑን የገለጹት ኢትዮጵያውያኑ ረሃብ ያደከመውን ሰውነታቸው ደግሞ በሊቢያ ታጣቂዎች ድብደባ የሚደርስበት መሆኑን ይገልጻሉ።

የህወሃት መንግስት ለኢትዮጵያውያኑ ሊደርስላቸው አልቻለም። ስልክ ቁጥሮችን በመስጠት ስደተኞቹ እንዲደውሉ ማስታወቂያ አስነግሮ ነበር። ሲደወል የሚመልስ ግን አልነበረም። ኢትዮጵያውያኑ ድረሱልን የሚለውን ጥሪያቸውን እያሰሙ ነው።