ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲነሱ ጥሪ ቀረበ

ሚያዝያ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ሜይ 2፣ 2015 ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ የተገኙት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መሪ አቶ ኦባንግ ሜቶና ታዋቂው ጸሃፊ እና ፖለቲካ ተንታኝ አቶ የሱፍ ያሲን፣ አገራችን ከገባችበት ችግር መላቀቅ የምትችለው  በአንድነት በመነሳት መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ የሱፍ ገዢው ፓርቲ ባመጣው የፌደራል ስርአት ሳንጣላ ተራርቀናል ያሉ ሲሆን፣ ልዩነታችን ለጥንካሬያችን መሰረት መሆኑን አውቀን በሰለጠነ መንገድ ተወያይተን በአንድነት እንነሳ ብለዋል።

አቶ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው በ ደቡብ አፍሪካ የደረሰውን ከማየት በላይ የሞት ሞት የውርደት ውርደት የለም ያሉ ሲሆን፣ ዜጎቻችን እየሞቱ መንግስት ዜግነታቸውን እያጠራሁ ነው ማለቱ፣ በአገራችን እንደዜጋ የማንቆጠርበት ደረጃ ላይ መደረሳችንን ያሳያል ብለዋል። ስደት የኢትዮጵያውያን እጣ ፋንታ ሆኗል አሉት አቶ ኦባንግ እጅ ለጅ ካልተያያዝንና ካልታገልን ከሚመጣው አደጋ ራሳችንንም ሆነ አገራችንን መታደግ አንችልም ብለዋል።

የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን አሰፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምትገኝበትን የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የጎሳና የሃይማኖት ቀውስ እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ በመድረሱ ሳቢያ የዜጎችና የሀገር ህለውና አደጋ ላይ ወድቋል ብለዋል።