(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 24/2011)ከታንዛኒያ ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ ላይ የነበሩ 14 ኢትዮጵያውያን በመኪና ውስጥ ታፍነው መሞታቸው ተሰማ።
በምስራቃዊ ታንዛኒያ ግዛት ሚንሱ በተባለ ቦታ በመኪና ውስጥ ሞተው ከተገኙት 14ቱ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ሌሎች 12 ኢትዮጵያውያንም በሕይወት የተገኙ ሲሆን ለህክምና ሆስፒታል መላካቸው ተመልክቷል።
በምስራቅ ታንዛኒያ ግዛት የሞሮጎሮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ዊልብሮድ ሙታፍንግዎ ለታንዛኒያው IPP ሚዲያ በሰጡት መግለጫ በህይወት ከተረፉት 12ቱ ኢትዮጵያውያን 5ቱ ወዲያውኑ ህክምና እንደተደረገላቸውና ሌሎች 7 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ግን ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው አክለዋል።
ታንዛኒያን አቋርጠው በማሊ ወይንም በዛምቢያ አቋርጠው ደቡብ አፍሪካ ለመድረስ በመጓዝ ላይ የነበሩት ኢትዮጵያውያን በመኪና ውስጥ ታፍነው ህይወታቸው ያለፈው ዕሁድ ዕለት መሆኑም ተመልክቷል።
በህገወጥ መንገድ ታንዛኒያ የገቡትና ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ ላይ የነበሩት ስደተኞችና በህይወት ለተረፉት ኢትዮጵያውያን ህክምና የሰጠው የምሮጎሮ ሆስፒታል ተጠባባቂ ኦፊሰር ዶክተር ፍራንሲስ ሰሞዊን ኢትዮጵያውያኑ ህይወታቸው ያለፈው በመታፈን መሆኑን አረጋግጠዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በግንቦት 2017 በተመሳሳይ የ8 ኢትዮጵያውያን አስከሬን በአንድ መኪና ውስጥ መገኘቱንም ዘገባው አስታውሷል።