ኢሳት (ሚያዚያ 28 ፥ 2008)
የደቡብ አፍሪካና የኬንያ መንግስታት ወደ ሃገሪት በህገ-ወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉ በርካት ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አርብ አስታወቁ።
የደቡብ አፍሪካ የፀጥታ ሃይሎች ጀርዎስተን ተብሎ በሚጠራው ምስራቃዊ ከተማ ሃሙስ ምሽት ባካሄዱት አሰሳ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 96 የሶማሊያ፣ የሞዛምቢክ፣ የዚምባብዌና የናይጀሪያ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ለእስር ከተዳረጉት መካከልም ስድስቱ ሴቶች ሲሆኑ እድሜያቸውም ከ19 ኣስከ 52 አመት ድረስ ድረስ መሆኑን የከተማዋ ፖሊስ ቃል-አቀባይ ዊልፍሪድ ጋሳጎ ኒውስ 24 ለተሰኘ ጋዜጣ አስረድተዋል።
የሃገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ባካሄዱት አሰሳ በቁጥጥር ስር የዋሉት ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን እና ሌሎች ሃገራት ተወላጆችም ወደ ደቡብ አፍሪካ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ክስ እንደሚመሰረትባቸው ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ የኬንያ መንግስት በየጊዜው ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ለመቆጣጠር አዳዲስ የቁጥጥር ኬላዎች (ጣቢያዎች) ቢያቋቁምም ወደ ኬንያ የሚገቡ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ እልባት አለመኘቱን አርብ አስታውቋል።
የኬንያ የጸጥታ ሃይሎች ሃሙስ ምሽት ወደባዋማ ከተማ ሞምባሳ ሲያቀኑ ነበር ያላቸውን ሶስት ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ዘ-ስታር የተሰኘ ጋዜጣ አርብ ዘግቧል።
የሃገሪቱ የፀጥታ ሃይሎች ከሳምንት በፊት ከ20 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያንን ለእስር ዳርገው እንደነበር ያወሳው ጋዜጣው የኢትዮጵያውያኑ ስደት በየዕለቱ መቀጠሉንም አመልክቷል።
የሊኮኒ አስተዳደር ፖሊስ ሃላፊ የሆኑት ዊሊ ሲምባ ሶስቱ ኢትዮጵያውያ ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ክስ እንደሚመሰረትባቸው ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ለመሸሽ በየዕለቱ ቁጥራቸው በርካታ የሆን ኢትዮጵያውያን ጦርነት እልባት ወዳላገኘባት የመንና የተለያዩ ሃገራት በመሰድድ ላይ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽንና የለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅ (IOM) በተደጋጋሚ ሲገልፁ መቆየታቸውም ያወሳል።