ጥር ፲፰ ( አሥራ ስምንት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ በሕገወጥ መንገድ ወደ ዝንባብዌ ገብተዋል ተብለው በእስር ላይ የነበሩ 34 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን የአገሪቱ ፍርድ ቤት ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ሲል ውሳኔ አስተላልፎአል።
በምስራቃዊ ዝንባቢዌ ማሮንዴራ እርሻ ማሳ ውስጥ ከተደበቁበት በፀጥታ ሃይሎች የተያዙት ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ምንም ዓይነት ሕጋዊ የጉዞ ሰነድ አለመያዛቸውን የስደተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ስደተኞች እስካሁን ድረስ በእስር ሊቆዩ የቻሉት አስተርጓሚ ማግኘት ባለመቻሉ መሆኑንም በምክንያትነት ቀርቧል። በእስር ላይ የሚገኙት ሁሉም ስደተኞች በሙሉ ወንዶች ሲሆኑ 4ቱ የ11 እና 12 ዓመት ታዳጊዎች ናቸው። ኢትዮጵያዊያኑን ስደተኞችን ለመያዝ የእርሻ ማሳው በፖሊስ መቃጠሉን እና ስደተኞቹን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመለስ የሚያስችል የጉዞ ሰነድ እስኪቀርብ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ በእስር ሊቆዩ ይችላሉ ሲል ኒውስ ዴይ አክሎ ዘግቧል።
ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በተለያዩ አገራት እስር እና እንግልት ሲደርስባቸው በኤንባሲዎች እና ቆንስላዎች ምንም ዓይነት ከለላ አያገኙም። በኩዌት ሞት የተፈረደባት ኢትዮጵያዊት ሕጋዊ ጠበቃ እና የሕግ ማማከር አገልግሎት ሳታገኝ ሕይወቷ ማለፉ ይታወሳል።