መጋቢት ፳፯ (ሃይ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት 7 አመታት 11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንዳገኘ በተደጋጋሚ መናገሩ ይታወቃል። የአለማቀፍ የገንዘብ ተቋም ወይም አይኤም ኤፍ የኢትየጵያ እድገት የተጋነነ ነው በማለት እድገቱ ከ6 እስከ 7 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል በመግለጥ የመንግስትን መከራከሪያ ውድቅ ሲያድርግ ቆይቷል። ገዢው ፓርቲ የኢኮኖሚ እድገቱ የመጣው መንግስት የውጭ ንግድን ማእከል ያደረገ ፖሊሲ ቀርጾ በመንቀሳቀሱ መሆኑን ይገልጣል። የብሄራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳው ከሆነ ግን የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እድገት መሰረቱ የወጭ ንግድ ሳይሆን በውጭ አገር የሚኖረው በተለምዶ ዲያስፖራ እየተባለ የሚጠራው ኢትዮጵያዊ ነው።
በአለፉት 7 አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ ካፈሰሱት የውጭ እና የአገር ውስጥ ድርጅቶች መካከል የህንድ፣ የቻይና ፡ የሼክ ሙሀመድ አላሙዲን እና የህወሀት ንብረት የሆነው ኢፈርት ኩባንያዎች ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ ኩባንያዎች ቡና፣ ጫት፣ ሩዝ፣ ሰሊጥ እና ሌሎችንም የቅባት እህሎችን፣ የቆዳና የቁም ቀንድ ከብቶችን እንዲሁም ወርቅን ጨምሮ ሌሎችን ማእድናት ለውጭ ገበያዎች ይልካሉ። እነዚህ ኩባንያዎች በተያዘው የኢትዮጵያ የበጀት አጋማሽ አመት ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ አገር ልከው አገሪቱ ያገኘችው ገቢ 1 በሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር ወይም 23 በሊዮን ብር ሲሆን፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ የበጀት አመት ለዘመዶቻቸው ካለኩት ገንዘብ አገሪቱ ያገኘችው 1 ቢሊዮን 7 መቶ ሚሊዮን 400 ሺ ዶላር ወይም 32 ቢሊዮን ብር ነው። ዲያስፖራው የላከው ገንዘብ ከውጭ ንግድ ከተገኘው ጋር ሲነጻጸር ከ5 እስከ 9 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው።
የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ እድገቱ ቀዳሚ መሰረት የመንግስት ፖሊሲ መሆኑን ከመናገር ባለፈ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን አስተዋጽኦ አንድም ቀን ገልጦ አያውቅም። በብሄራዊ ባንክ መረጃ መሰረት በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውን ገንዘብ ወደ አገራቸው መላክ ቢያቆሙ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ክፉኛ ይናጋል። የኢትዮጵያ መንግስት የዲያስፖራ ፖሊሲ በመቅረጽ ዲያስፖራውን ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርገው ዲያስፖራው ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትና ለመንግስት ህልውና ቁልፍ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ነው ሲሉ ጉዳዩን በቅርብ የሚያጠኑ አንድ ባለሙያ ለኢሳት ገልጠዋል።
ዲያስፖራው ያልተዘመረለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሞተር ነው የሚሉት ባለሙያው ፤ዲያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ የሚልከው የውጭ ምንዛሬ የውጭ አገር መንግስታት ከሚሰጡት እርዳታ ጋር ሲተያይ ከፍተኛ ብልጫ ያለው በመሆኑ ለመንግስት አስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ ሆኗል ሲሉ ያክላሉ። በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ገንዘብ የመለስ መንግስት በአገር ውስጥ ከሚሰበሰበው ታክስ መጠን ጋር ተስተካካይ መሆኑንም ባለሙያው ይናገራሉ።
ዲያስፖራው በመንግስት ላይ ሊፈጥር የሚችለው ተጽእኖ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ መሆኑን የገለጡት ባለሙያው፣ ይህ የኢኮኖሚ ተጽእኖ ወደ ፖለቲካ ተጽኖ የሚቀየርበት ስርአት አለመዘርጋቱንም አልሸሸጉም። ዲያስፖራው ገንዘቡን ለዘመዶቹ የሚያስተላልፍበት አማራጭ መንገድ ስለሌለው በመንግስትን ላይ በበቂ ሁኔታ ተጽእኖ ማሳረፍ አይችልም፣ ለዘመዶቹ ገንዘብ መላክ ማቋረጥ ማለትም በዘመዶቹ ህይወት ላይ መፍረድ መሆኑን ያውቃል ፣ በዚህም የተነሳ ያለው አማራጭ ባለው የገንዘብ አላላክ ስርአት ተጠቅሞ ዘመዶቹን መርዳት ነው፣ ከመንግስት ተጽእኖ ውጭ ያሉ የአላላክ ስርአቶች ቢኖሩም ጠንካራ አይደሉም ሲሉ አብራርተዋል። ዲያስፖራው መንግስት በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርአትን እንዲዘረጋ፣ የሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብር እና የህግ የበላይነትን እንዲያስጠብቅ በአጠቃላይ መንግስት የፖለቲካ ለውጥ እንዲያደርግ የማያስችል ጉልበቱ ቢኖረውም አንድ ሆኖ አንድ ወጥ የመቆጣጠሪያ መንገድ ለመፍጠር ባለመቻሉ ጉልበቱን ሲጠቀምበት እንደማይታይ ባለሙያው አክለው ተናግረዋል።
________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide