በሰሜን ጎንደር ዞን በታች አርማጭሆ ወረዳ በሲናር በረሃ የኢትዮጵያን የእርሻ መሬት ለመውሰድ በተንቀሳቀሱ የሱዳን ወታደሮች ላይ ተኩስ የከፈቱት ኢትዮጵያዊ አርሶአደሮች 5 የሱዳን ወታደሮችን ገድለዋል።
ሰኔ 25 ቀን 2008 ዓም የሱዳን ወታደሮች የጓንግን ወንዝ ተሻግረውና አንድ የእርሻ ካም አቃጥለው ጦርነት ሲከፍቱ ፣ በተለይ ጎዳና አምዴ የተባለው ወ ጣት አርሶአደር እና አብረውት የነበሩት 5 የሱዳን ወታደሮችን ገድለው 3 ክላሽንኮቭ እና አንድ መትረጊስ ማርከው ወታደሮቹ እንዲሸሹ አድርገዋል።
የሱዳን ወታደሮች ብዙዎችን ወታደሮች የገደለውን ወታት ጎዳናን ከመሸገበት ቦታ ሲወጣ ጠብቀው በመተኮስ ገድለውታል። ይሁን እንጅ የወጣቱን አስከሬን ለመውሰድ አለመቻላቸውንና የአካባቢው ህዝብ ጥቃቱን በማጠናከሩ ወታደሮቹ እንዲያፈገፍጉ ማድረጉን የሟች ዘመዶች ገልጸዋል ።
የወጣት ጎዳና የቀብር ስነስርዓት በጎንደር ከተማ ዮሃንስ ቤ/ተ ክርስቲያን የተፈጸመ ሲሆን፣ የአካባቢው ህዝብ በድርጊቱ ተበሳጭቶ ቁጣውን በመግልጽ ላይ ነው። በአካባቢው የነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች በሱዳን ወታደሮች ላይ ምንም አይነት እርምጃ ባለመውሰዳቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የኢህአዴግ መንግስትና የሱዳን መንግስት ተመሳጥረው የፈጸሙት ነው እያለ ነው።
የሱዳን መንግስት በቅርቡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር በአካባቢው ማስፈሩን ነዋሪዎች ይናገራሉ። መሬቱ ቀድም ብሎ በኢህአዴግ መንግስት እንደተሰጣቸው የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ህዝቡ በራሱ ጉልበት እስካሁን መሬቱን ይዞ መቆየቱን ይገልጻሉ።
የሱዳንና የኢህአዴግ መንግስት ከውስጥ እና ከውጭ ሆነው የአካባቢውን ህዝብ በማዳከም መሬቱ ለሱዳን እንዲሰጥ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል በማለት የሚከሱት ነዋሪዎች፣ የአካባቢው ህዝብ መሳሪያ እንዲያስረክብ በተደጋጋሚ የተደረገው መኩራ አለመስራቱንም ያክላሉ።
ድርጊቱን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት መሰፈኑንም ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል።