ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አሁንም ወደ የመን መፍለሳቸውን እንዳላቆሙ ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት አሳታወቀ

ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መነሻቸውን ከሶማሊያ የባሕር ዳርቻዎች በማድረግ በሕገወጥ መንገድ ሕይወታቸውን ለአደጋ አልጋልጠው በጦርነት ሰላሟ ወደራቃት የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ቁጥር መጨመሩን ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት በምህጻረ ቃል /UNHCR/ አስታውቋል። ባለፈው ዓመት ብቻ ከ70 ሺ በላይ አዲስ ስደተኞች የመን መግባታቸውን የገለጸው ድርጅቱ፣ ጥቂት የሶማሊያ ዜጎች ሲገኙበት አብዛኞቹ ስደተኞች ኢትዮጵያዊያን ናቸው። 88 ስደተኞች በባሕር ውስጥ ሰጥመው መሞታቸውንም ድርጅቱ አስታውቋል።
የመንን ለመሸጋገሪያነት በመጠቀም ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት ለስራ ፍለጋ የሚመጡት ስደተኞች የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙባቸውና በየመን ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የምግብ እና የጤና አቅርቦት የተሟላ ባለመሆኑ የረድኤት ድርጅቶች አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንዳሉም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ሁለት አሃዝ አድጋለች እየተባለ በየቀኑ ቢነገርም ፣ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በአራቱም ማእዘናት መፍለሳቸውን አለማቆማቸው ሲታይ የአገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ ትሩፋቶች ለሕዝቡ እንደልደረሰ ያመላክታል ሲሉ የሙያው ጠበብት ይገልጻሉ።