ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በማላዊ እስር ቤትና በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በስቃይ ላይ ናቸው

ግንቦት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አገር አቆራርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሲሞክሩ በማላዊ መግቢያና መውጫ ድንበሮች አካባቢ የተያዙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በእስር ቤትና በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በስቃይ ላይ እንደሚገኙ ተዘገበ። ማላዊ በሚገኘው ዲዛካ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UNHCR) ስር ባሉት የመጠለያ ጣቢያዎች ካሉ 24 ሽህ ስደተኞች ሲኖሩ፣ ከእነዚህ መካከል በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ይገኙበታል ብሎአል።
በቂ የሆነ የምግብ አቅርቦት ባለመኖሩና በተፋፈገ ሁኔታ ውስጥ ለመኖር በመገዳዳቸው ስደተኞቹ ላይ የጤና ችግሮች ተከስቷል። በአገሪቱ ውስጥ ተዘዋውረው የመስራት እድል ለስደተኞቹ ባለመፈቀዱም አማራጭ አጥተው በስቃይ እንደሚኖሩና ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ዘሜይል ኤንድ ዘጋርዳኢያን ዘግቧል። ከዋና ከተማዋ ሊንግ ዌ 45 ኪሎ ሜትር ከሚርቀው ዲዛካ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለማምለጥ ሲሞክሩ 9 የኮንጎ ዲሞክራቲክ ዜጎች በፓሊስ ተይዘዋል።