ታኀሳስ ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በትውልድ ኢትዮጵያዊ እና በዜግነት ፊላንዳዊ የሆኑት ከፍተኛ የእርሻ ሳይንቲስት ዶ/ር የሺጥላ ደገፉ የክብር ሜዳልያውን የተሸለሙት ባለፈው ቅዳሜ ፣ ፊንላንድ 97ኛ አመት የነጻነት በአሉዋን ባከበረችበት ወቅት ነው።
ዶ/ር የሺጥላ ዕጽዋት ከየትና እንዴት በሽታ እንደሚይዛቸው፤ እንዴትስ በውስጣቸው እንደሚተላለፍና በራሳቸውም እንዴት እንደሚከላከሉ ከ23 ዓመታት ምርምር በሁዋላ ሂደቱን ለመጀመሪያ ጊዜ በማግኝታችው ነው። ፊንላንድ መሠረታቸው ወይንም ዘራቸው ሳያግዳት ዜጎቿን እንደምታከብር በሚያሳይ መንገድ፤ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ሳውሊኒ ኒስቶ የሜዳልያ ሽልማቱን አበርክተውላቸዋል።
በተለይም ባለፉት አሥር ዓመታት የድንች ዘር ላይ በማተኮር በውስጡ በሽታ የሚያስተላልፍበትን መንገድ በማግኘታቸው፡ ከሥር መሠረቱ ለመከላከል የሚያስችል በመሆኑ፡ በተለይም ድንችንና ሌሎች ዕጽዋቶችን ወደ ተለያዪ ምግቦች የሚቀይሩ ኩባንያዎችም ብዙ ሃብት የሚያፈሱበት መስክ በመሆኑ፡ ኩባንያዎች እንዲጠናከሩ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው በከፍተኛ ከበሬታ ነው የታየው።
ዶ/ር የሺጥላ ክሮስ ኦፍ ዘ ኦርደር ኦፍ ዘ ሁዋይት ሮዝ ኦፍ ፊንላንድ የተባለውን ከፍተኛ ሽልማት ተሸልመዋል።ዶ/ር የሺጥላ የመጀመሪያ ድግሪያችውን ያገኙት ከቀድሞው ዓለማያ የእርሻ ምሩቅ ኮሌጅ በ1982 ዓም ሲሆን፤ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪዎቻቸውን ደግሞ ያገኙት ከሂለሲንኪ ዩኒቨርሲቲ ፊንላንድ ውስጥ ነው።
መጀመሪያ በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ በመምህርነት በከፍተኛ ሌክቸረርንት ደረጃ ለአጭር ጊዜ አገልግለዋል። ተሸላሚው ስለሥራችው ሲናገሩ፡ የጥናታችው ውጤት ለገበሬውና ለአጠቃላይ ኅብረተስብ እጅግ ጠቃሚ ነው ይላሉ።