ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ወደየመን እየጎረፉ ነው ተባለ

ኢሳት ዜና (ሃምሌ 9 2007)

ግጭት ወደአለበት የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ አሳስቦት እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትናንት ረቡእ ገለጸ ።

በየመን ያለው የጸጥታ ሁኔታ አደገኛ ቢሆንም በብዙ ሺ  የሚቆጠሩት ስደተኞች አሁንም ድረስ ወደ ሀገሪቱ እየገቡ መሆናቸውን ረቡእ ከጄኔቫ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ የሰጡ የደርጅቱ ሀላፊዎች አስታውቀዋል።

ከኢትዮጵያኑ በተጨማሪ የሶማሊያ ተወላጆች ወደየመን እየተሰደዱ እንደሆነ የገለጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ሆኖ እንደሚገኝ አመልክቷል ።

በየመን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ተወካይ የሆኑት ጆሀንስ ቫን ዳር ከመጋቢት ወር ማጠናቂያ ጀምሮ 10 ሺ ስደተኞች ወደ የመን መሰደዳቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ወደ ሀገሪቱ ስለሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን እና ሶማሊያዊያን ጉዳይ ግራ ተጋብተናል የሚሉት ተወካዩ ስደተኞቹ የየመንን ወቅታዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ አስገብተው ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

በየመን የተቀሰቀሰው ግጭት ተከትሎ 1 ሺ 670 ሰዎች መገደላቸውን እና ወደ 4 ሺ የሚጠጉ ሰዎችም ጉዳት እንደደረሰባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።

የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ወደየመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በማሻቀብ ላይ መሆኑን ሲዘግቡ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጲያውያንም በተጨማሪ አሁንም ድረስ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን እየጎረፉ መሆናቸውን ለኢሳት አስረድተዋል።

የችግሩ አሳሳቢነትን በመረዳትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያና በሶማሊያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ለመስጠት መወሰኑን ሀላፊዎች ገልጸዋል።