ኢትዮጵያኖችን ከየመን ወደ አገራቸው ለመመለስ የበረራ ፈቃድ እየጠበቀ መሆኑን አለማቀፍ የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ

ሚያዝያ ፪(ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በእንግሊዝኛ IOM በመባል የሚታወቀው ድርጅት ባወጣው ዘገባ በሚቀጥሉት ቀናት ከየመን ሰንአ ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ካርቱም ተከታታይ በረራዎችን ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቆ የበረራ ፈቃድ

በመጠባበቅ ላይ ነው።

አይ ኦ ኤም የበረራ ፈቃዱን የሚጠይቀው ከማን እንደሆን አላስታወቀም። ምን ያክል ኢትዮጵያውያን ለመመለስ ፈቃደኛ መሆናቸውንም አላስታወቀም። ይሁን እንጅ በየመን የሚገኙ ስደተኞች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቋል። ድርጅቱ ለስደተኞች

መጠነኛ እርዳታ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጾ፣ ስደተኞች በሳውድ አረቢያ በሚመራው የአየር ድብደባ እየተጎዱ መሆኑንም ጠቁሟል። ጦርነቱን ተከትሎ ምን ያክል ኢትዮጵያውያን እንደሞቱና እንደቆሰሉ በትክክል የታወቀ ነገር የለም።

ከ100 ሺ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት የመን፣ ወደ አገራቸው ለመመለስ በኢትዮጵያ ኢምባሲ በኩል የተመዘገቡት ሰዎች ቁጥር ከ2 ሺ አይበልጥም። በየመን የሚካሄደው ጦርነት በቶሎ ካልበረደ፣ ሰብአዊ ቀውሱ እየከፋ ሊሄድ እንደሚችል የእርዳታ ድርጅቶች

በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓኪስታን ፓርላማ በየመን በሚኬደው ጦርነት ገለልተኛ ሆኖ ለመታዘብ ውሳኔ አሳልፏል። ቀድም ሲል የፓኪስታን መንግስት ከሳውድ አረቢያ ለቀረበለት የአየር ሃይል፣ የባህር ሃይልና የእግረኛ ወታደር ድጋፍ መልስ እንደሚሰጥ ቢያስታውቅም፣ የአገሪቱ ፓርላማ ግን ውሳኔውን በመቀልበስ ገለልተኛ ሆኖ ለመታዘብ መወሰኑን ገልጿል።

የሃውቲ ሚሊሺያዎችን ትደግፋለች በሚል የምትከሰሰው ኢራን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ ፓኪስታን ልካለች። የፓኪስታን ውሳኔ ሳውድ አረቢያን ሲያስከፋ ኢራንን የሚያስደስት ይሆናል።

የኢህአዴግ መንግስት በሳውድ አረቢያ የሚካሄደውን የአየር ጥቃት መደገፉ ይታወቃል።