ሚያዝያ ፫ (ሦስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜናዊ ምስራቅ አፍሪካ አገራት በተከሰተ ድርቅ 11 ሚሊዮን የኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ዜጎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ በተባበበሩት መንስግታት ድርጅት የሕጻናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ እና የዓለም የምግብ ድርጅት በጋራ አስታውቀዋል።
ድርቁ በደቡብ ሱዳን ከ100 ሺ በላይ ነዋሪዎችን ሲያጠቃ፣ ከ20 ሺ በላይ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው። በደቡብ ሱዳን ከድርቁ በተጨማሪ የእርስበርስ ጦርነቱ በነዋሪዎቹ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ችግር መደቀኑን በዓለም የምግብ ድርጅት /WFP/ የምስራቅ እና ማእከላዊ አፍሪካ ዳሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ቫሌሬየ ጉዋርኔሪ ገልጸዋል።
በዩኒሴፍ የደቡብ እና ምስራቅ አፍሪካ ዳሬክተር የሆኑት ለይላ ፓካላ በበኩላቸው ”ድርቁን ተከትሎ በተፈጠረ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት በአካባቢው የኮሌራ በሽታ መቀስቀሱንና በበሽታውም አያሌ ሕጻናት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ገልጸዋል። “ሕጻናቱ በምግብ እጥረት ብቻ ሳይሆን የተበከለ ውሃ በመጠጣታቸው ምክንያት በውሃ ወለድ በሽታዎች ተጠቅተው እና ክትባታቸውን በማቋረጣቸው ለሞት ተዳርገዋል። በኮሌራና በወባ በሽታ ሲጠቁ ሕይወታቸውን ለመታደግ የሚያስችል ምንም ዓይነት የጤና አገልግሎቶች አያገኙም” ሲሉም አክልዋል።
”ድርቁ በሶማሊያ አድማሱን እያሰፋ ቢሆንም በኢትዮጵያም በከፋ ሁኔታ የቤተሰቦችን ሕይወት እያቃወሰ ይገኛልም” በማለት ድርቁ በአካባቢው ነዋሪዎች ሕይወት ላይ ሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉን ገልጸዋል።
ሶማሊያ ውስጥ 440 ሺ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ከአምና ጀምሮ በድምሩ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሶማሊያዊያን ተፈናቃይ መሆናቸውን ዩኒሴፍ አስታውቋል። 350 ሺ በላይ ሶማሊያዊያን እና 1.9 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናዊያን በኢትዮጵያ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለዋል። ከእነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ ከ50 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ሕጻናት እና ሴቶች ሲሆኑ በውሃ እና ምግብ እጥረት ምክንያት ለከፋ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል።
ተፈናቃይ ሕጻናት ከወላጆቻቸው መለየትንና ጾታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ ለተለያዩ ማሕበራዊ ቀውሶች የተጋለጡ ሲሆን፣ በሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን የጾታ ትንኮሳዎች ተባብሰው መቀጠላቸውም ተገልጿል። ይህን ለማስቀረት እና ሕጻናት ከወላጆቻቸው ተነጥለው እንዳይሰደዱ የማድረግ ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን ለይላ ፓካላ አክለው ተናግረዋል።
የዓለም የምግብ ድርጅት እና ዩኒሴፍ እንዳሉት በድርቅ ምክንያት ለከፍተኛ የርሃብ ጉዳት ተጋላጭ ለሆኑት የቀጠናው አገራት የሚውል የረድኤት እርዳታው በታሰበው መጠን አልተገኘም። ይህን ተከትሎ በእነዚህ አገራት ረሃቡ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተመድን ጠቅሶ ዠንዋ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መንግስትን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ ደግሞ በድርቅ የተጠቁ ወገኖች ቁጥር ከሁለት ወራት በፊት ተገልጾ ከነበረው እንደሚልቅና አዲስ መረጃ ይፋ እንደሚደረግ ገልጿል። በተለይ በኦሮምያ፣ ደቡብ፣ ሶማሊና አማራ ክልሎች በድርቅ የተጎዱ ወገኖች ቁጥር እንደሚጨምር የገለጸው ድርጅቱ፣ በኦሮምያ እርዳታ እየተደረገላቸው ካሉት 2 ሚሊዮን ዜጎች በተጨማሪ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል።
የምግብ ወጋ እየናረ መምጣትም በከተሞች ለሚኖሩት ዜጎችም ፈተና እየሆነ ነው ተብሏል።