ሰኔ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዓመታዊው የአገራት ሰላምና ጸጥታ የሰፈነባቸውና ለሰው ልጆች ደኅንነት አስጊ የሆኑ አገራት ጥናት የደረጃ ሰንጠረዥ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ በዓለማችን ላይ ያሉ ለወደፊቱ እንደ አገር ለመቀጠል ከፊት ለፊታቸው ሥጋት ከተደቀነባቸው 25 አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች። በዓመታዊው የአገራት የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት ሰላምና ጸጥታ የሰፈነባቸው ለዜጎች ምቹ የደኅንነት ዋስትና ያላቸው በመባል የስካንዲኒቪያን አገራት በቀዳሚነት ይመራሉ።
ኢትዮጵያ ከሃያ አምስቱ አገራት 24ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን 64 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ እድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች ውስጥ እንደሚገኙና በከፍተኛ ደረጃ የሕጻናት ሞት ከሚከሰትባቸው 33 የዓለማችን አገራት ተርታ እንደምትመደብም ጥናቱ አመላክቷል።
ባለፈው ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ከ400 ሽህ በላይ ዜጎቿ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። ይህም ለወደፊቱ እንደ አገር ለመቀጠል ከፊት ለፊታቸው ከፍተኛ የሆነ የደኅንነት ሥጋት ከተደቀኑባቸው አገራት ተርታ ኢትዮጵያ እንደምትገኝ ጥናቱ አመልክቷል።
ሁለቱ ጎረቤት አገራት ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ሲመሩ መሃከለኛው አፍሪካ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ቻድ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታንና አይቲ ከአንድ እስከ አስር ያለውን ደረጃ በቅደምተከተላቸው ይዘዋል።