ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ ያሉት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናትኒያሁ መንግስታቸው በሽህዎች የሚቆጥሩ ኢትዮጵያውያን ይሁዲዎችን  እስራኤል ሀገር ወደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ለመውሰድ እንደሚፈልግ ገለጹ።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ  አያቶቻቸውና አባቶቻቸው  አይሁዳውያን  እንደሆኑ የሚያምኑ በትንሹ 9ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን  ወደ እስራኤል ለመጓዝ ለዓመታት እየጠበቁ ይገኛሉ።

ናትኒያሁ ከኢትዮጵያው አቻቸው ጋር በሰጡት መግለጫ  የአይሁድ ኢትዮጵያኑ ጉዞ በቅርቡ እንደሚከናወን  ገልጸዋል። ይሁንና መቼ እንደሚሆን ትክክለኛውን የጊዜ ሰሌዳ አልተጠቀሱም። “አይሁድ ኢትዮጵያውያንን ወደ እስራኤል የመመለሱን ጉዳይ እየሰራንበት ነው፤ያን ለማድረግ ቁርጠኝነቱ አለን። በቤተሰብ መቀላቀል ሂደቱ  የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ እያሟላን ነው። ይህ የሚሆነው ለወደፊት አይደለም።በወቅቱ በጀት አማካይነት አሁን ነው የሚፈጸመው” ብለዋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ኒያትኒያሁ።

 

አትዮጵያውያን  እስራኤላውያኑን  የማጓጓዙ ዘመቻ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1984 ዓመተ ምህረት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በትንሹ 130 ሺህ  ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በእስራኤል ይኖራሉ።

የናትኒያሁ መንግስት ኢትዮጵያውያኑ ይሁዲዎችን ከተቀረው የእስራኤል ማህበረሰብ ጋር በተሟላ ሁኔታ በማቀናጀቱ ረገድ ተገቢውን ሥራ አላከናወነም በሚል  ጠንካራ ትችት እየቀረበበት ይገኛል።

ደርሶብናል በሚሉት መድሎና መገለል ሳቢያ ባለፉት ወራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናትኒያሁ በጉብኝታቸው  ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ በአፍሪካና በእስራኤል መካከል ጠንካራና ቅርብ የሆነ ግንኙነት እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል።

የግብርናና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅን በማሻሻል ረገድ የሁለትዮሽ ስምምነት መፈረሙንም የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።