ኢትዮጵያንና ግብፅ ለመሸምገል እስራዔል ጣልቃ እንድትገባ ሃሳብ ያቀረቡት የግብፅ የፓርላማ አባል ከፓርላማ አባልነታቸው ተነሱ

ኢሳት (የካቲት 25 ፥ 2008)

በቅርቡ የእስራዔል መንግስት ኢትዮጵያንና ግብፅ በአባይ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባት ለመሸምገል ጣልቃ እንዲገባ ሃሳብን ያቀረቡ የግብፅ የፓርላማ አባል ከፓርላማ አባልነታቸው ተነሱ።

የሃገሪቱ የፓርላማ አባላት የፓርላማ አባል የሆኑ ቶፊክ ኦካሻ ከእስራዔል አምባሳደር ጋር ያደረጉት የእራት ግብዣ ስነ-ስርዓት የሃገሪቱን የፓርላማ ስርዓት የጣሰ ተግባር ነው በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ማቅረባቸው ታውቋል።

ይህንንም ተከትሎ ለግብፅ ፓርላማ የቀረበ ሃሳብ የፓርላማ አባሉ ከአባልነታቸው እንዲሰናበቱ የጠየቁ ሲሆን 403 የፓርላማ አባላትም ቶፊክ ኮካሻ እንዲሰናበቱ ድምፅ መስጠታቸውን አፍሪካ ፕሬስ ኤኔርጂ ሲ ሃሙስ ዘግቧል።

የሃገሪቱ የፓርላማ ህግ መሰረት አድርጎ ተካሄዷል በተባለው በዚሁ ስነ-ስርዓትም የፓርላማ አባሉ በአብዛኛው ድምፅ እንዲሰናበቱ መደረጋቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የግብፁ የፓርማ አባልና የአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤት የሆኑት ቶፊክ ኦካሻ በግብፅ የእስራዔል አምባሳደር የሆኑትን ሃይም ኮረንን በመኖሪያ ቤታቸው ለእራት በመጋበዝ በአባይ ግድብ ዙሪያ መምከራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የፓርላማ አባሉ እስራዔል የሽምግልና ሚናን በመጫወት በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል እልባት ያላገኘውን የአባይ ግድብ ግንባታ ልዩ-ትክረት ሰጥታ ጣልቃ እንድትገባ መጠየቃቸውንም ታውቋል።

ይሁንና፣ የፓርማ አባሉ የተከተሉት አካሄድ ከስነ-ስርዓት ውጭ ነው በማለት የግብፅ ፓርላማ ከረቡዕ ጀምሮ ቶፊክ ኦካሻን ያሰናበተ ሲሆን ድርጊቱም በሃገሪቱ ታሪክ መነጋገሪያ ሆኖ ይገኛል።

የፓርላማ አባሉ መታገድን ተከትሎም በቶፊክ ኦካሻ ባለቤትነት ይተዳደር የነበረው አል-ፋርን የቴሊቪዥን ጣቢያ ስርጭቱን በማቋረጥ ለሽያጭ መቅረቡንም የዜና አገልግሎቱ አክሎ ዘግቧል።

ስርጭቱን ያቋረጠውን የቴለቪዥን ጣቢያው ሁሉንም ፕሮግራሞች እንዳቆመ በመግለጽ ለሽያጭ መቅረቡን ይፋ እንዳደረገም የሃገሪቱ መገናኛ ብዙይሃን ሃሙስ ባቀረቡት ዘገባ አመልክቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ የእስራዔልም ሆን የኢትዮጵያ መንግስት የሰጡት ምላሽ የለም።