ኢትዮጵያና ኬንያ በጸጥታ ጉዳይ ላይ እየተወያዩ ነው ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 15 ፥ 2008)

ኢትዮጵያና ኬንያ በሶማሊያ አሰማርተው ያለው የሰላም አስከባሪ ሃይል ተቀናጅቶ በሚሰራበት ጉዳይ ዙሪያ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች በኬንያዋ የወደብ ከተማ ሞምባሳ በመምከር ላይ መሆናቸው የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘገቡ።

መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገ አንድ የደህንነት ተቋም የሁለቱ ሃገራት ወታደሮች በሶማሊያ ባላቸው ተልዕኮ ተቀናጅተው ባለመስራታቸው ምክንያት በአልሻባብ ታጣቂ ሃይል ላይ ሲካሄድ የቆየው ዘመቻ ውጤት ሳያመጣ መቅረቱን መግለጹ ይታወሳል።

ኢትዮጵያና ኬንያ በታጣቂ ሃይሉ ላይ እያካሄዱ ያለው ዘመቻ የሁለቱ ሃገራት ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ እንደሚሆን ዘስታንዳርድ የተሰኘ ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ዘገባ አስነብቧል።

HIS ጄንስ የሚል መጠሪያ ያለው አለም አቀፉ የደህንነት ተቋም ኢትዮጵያና ኬንያ ተባብረው ሊሰሩ ባለመቻላቸው ምክንያት የሶማሊያ ታጣቂ ሃይል አልሻባብ በሞቃዲሾና በሌሎች አካባቢዎች እያደረሰ ያለው ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን አስታውቀዋል።

ከሁለቱ ሃገራት የትብብር ማነስ በተጨማሪ በርካታ የሰላም አስከባሪ ሃይልን አሰማርታ የምትገኘው ዩጋንዳ በፓርላማ ክፉኛ የባጀት እጥረት እየቀረበበት በመሆኑ በቅርቡ ከሶማሊያ ልትወጣበት የምትችል አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችልና እርምጃው በሰላም ማስከበሩ ስራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ሊያሳድር እንደሚችል ተገልጿል።

የኬንያ ባለስልጣናት በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝና የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ይህንኑ አበይት ጉዳይ ዋነኛ መነጋገሪያ እንደሚያደርጉት ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል ከወራት በፊት በኬንያ የሰላም አስከባሪ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ በወሰደው ጥቃት ከ100 በላይ ወታደሮችን እንደገደለ የሶማሊያው ፕሬዚደንት ማረጋገጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

ይሁንንና የሞቱባትን ወታደሮች ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥባ የምትገኘው ኬንያ በጥቃቱ ወታደሮቿ መገደላቸውን ግን ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ የሞቱ ወታደሮች ሃገሪቱ ሲደርሱ በቴሌቪዥን ለህዝብ መቅረቡም የሚታወቅ ነው።

አል-ሸባብ ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ በፈጸመው ጥቃት ወደ 60 የሚደርሱ ወታደሮችን እንደገደለ ቢገልጽም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሰለሞቱ ወታደሮች የሰጡት መረጃ የለም።

ይሁንና የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጥቃቱ ለሞቱ ቤተሰቦችና ለኢትዮጵያ መንግስት የሃዘን መግለጫን በማውጣት መልዕክት ማስተላለፉ ይታወሳል።