(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 15/2010) ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ያሳለፉትን ውሳኔ አሜሪካ አደነቀች።
የአሜሪካ መንግስት ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያና ኤርትራ ልዩነቶቻቸውን በማስወገድ ውይይት ለማድረግ የጀመሩትን ጥረት አድንቋል።
የአሜሪካ መንግስት ያወጣው መግለጫ ኢትዮጵያና ኤርትራ ባለፉት 20 አመታት የነበራቸውን አለመግባባት ለመፍታትና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መወሰናቸውን አድንቋል።
ቀደም ሲል የነበረው ግጭትና አለመግባባት በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ባለው የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ሰላም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉንም ጠቅሷል።
ከዚህ አኳያ አሁን ላይ ሃገራቱ ልዩነቶቻቸውን በማስወገድ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መወሰናቸው፥ ለሃገራቱ ህዝቦች ብሎም ለቀጠናውና ለመላው ዓለም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይረዳልም ነው ያለው።
መግለጫው ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መቀበሏን አሜሪካ ታደንቃለችም ብሏል።
ከዚህ ባለፈም የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያን መንግስት ውሳኔ በመደገፍና የሰላም ጥረቱን ለማገዝ፥ ከፍተኛ የሃገራቸውን ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መወሰናቸው የሚደነቅ መሆኑንም መግለጫው አንስቷል።
መግለጫው የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ወሳኝነት ያለው የመሪነት ተግባር መወጣታቸውንም ነው ያነሳው።
ሁለቱ ሃገራት በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈንና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና እንዳላቸውም አስታውሷል።
ከዚህ አንጻርም አሜሪካ ሁለቱ ሃገራት ሰላምን በማምጣት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ለሚያደርጉት ጥረት ማንኛውንም ድጋፍ እንደምታደርግም ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም ለአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊነት አሜሪካ ማንኛውንም ድጋፍ በማድረግ ትሰራለች ብሏል።