ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ወታደራዊ ሃይል ለማስፈር ተስማሙ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 11/2010)

ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ወታደራዊ ሃይል በድንበሮቻቸው አካባቢ ለማስፈር ተስማሙ።

ሁለቱ ሀገራት የጋራ ወታደሮቻቸውን የሚያሰፍሩት የአባይ ግድብ በሚገኝበት የቤንሻንጉል ክልልና በሱዳን የብሉናይል ግዛት ድንበሮች አቅራቢያ ነው።

በሱዳኑ የብሉናይል ግዛት ዋና ከተማ ዳማ ዚን የተፈረመው ስምምነት የተካሄደው በአፍሪካ ቀንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰተ ያለውን ውጥረት ተከትሎ መሆኑ ታውቋል።

በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ሀገራት ከወትሮው የተለየ ውጥረት መንገሱ ይነገራል።

ምክንያቱ ደግሞ የአካባቢው ሀገራት ጎራን የለየ ግንኙነት መጀመራቸውና በጥርጣሬ መተያየታቸው መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

ሱዳን ከግብጽና ከኤርትራ ጋር በድንበርና በፖለቲካ ጉዳዮች አተካራ ውስጥ መግባቷን ዘገባዎች በማመልከት ላይ ናቸው።

እንደሚባለው ሱዳንና ግብጽ እርስ በርስ መጠራጠር የጀመሩት የካርቱም መንግስት የቀይ ባህር ዳርቻ የሆነችውን የሱአኪን ደሴትን ለቱርክ አሳልፎ ሰጥቷል መባሉን ተከትሎ ነው።

ወትሮም ቢሆን በሃለይብ ወሰን በድንበር ምክንያት ከግብጽ ጋር ስትወዛገብ የነበረችው ሱዳ አናይ ግድብን አስመልክቶ ኢትዮጵያን መደገፏም ሁለቱን ሀገራት ይበልጥ እያወዛገባቸው ይገኛል።

ሱዳን በግብጽ የሚገኙ አምባሳደሯን እስከመጥራት ያደራሳትም ይሄው ጉዳይ ነው ተብሏል።

ሱዳን ከኤርትራ ጋር በፊት እየሻከረ የመጣ ግንኙነትም ከሀገሪቱ ጋር የሚያዋስናትን የከሰላ ድንበር መዝጋቷንና በአቅራቢያውም ወታደሮቿን ማስፈሯ ይነገራል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈውርቂ ግብጽን ባለፈው ጊዜ መጎብኘታቸውም የጉዳዩን እየጠነከረ መምጣት ነው ያመለከተው።

ሰላምም ጦርነትም የለም በሚባልበት የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይም በአካባቢው ውጥረቱ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

ኢትዮጵያና የአባይ ግድብን በተመለከተ ከግብጽና ሱዳን ጋር የሶስትዮሽ ግንኙነት ብትጀምርም በካይሮ መንግስት አለመስማማት ጉዳይ የልዩነት መንስኤ እስከመሆን ደርሷል።

ሱዳን የአባይ ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያን አቋም ትደግፋለች በሚል በግብጽ ጥርስ እንደተነከሰባት ነው የሚነገረው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ነው እንግዲህ ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ወታደሮቻቸውን በድንበሮቻቸው አቅራቢያ ለማስፈር የተስማሙት ኢትዮጵያና ሱዳን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በኩል ሰሞኑን ውይይት አካሂደዋል።

የሱዳኑ መከላከያ ሚኒስትርም በቅርቡ ኢትዮጵያን ጎብኝተው ሁለቱ ሀገራት የጋራ ወታደሮቻቸውን የአባይ ግድብ በሚገኝበት የቤንሻንጉል ክልልና በሱዳን የብሉናይል ግዛት ለማስፈር ተስማምተዋል ሚድል ኢስት እንደዘገበው።

በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ማንኛውም አካል ድንበሯን ተጠቅሞ ሱዳንን ቢያጠቃ በጋራ የመመከት ሃላፊነት አለባት።

ሱዳንም በተመሳሳይ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት በጋራ ለመመከት ነው የተስማማችው ተብሏል።

ስምምነቱ የተደረገውም የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች በብሉናይል ግዛት ዋና ከተማ ደማዚ ውይይት ካደረጉ በኋላ መሆኑ ተነግሯል።

ስምምነቱ ስለመደረጉም የብሉናይል ግዛት ዋና አስተዳዳሪና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዝዳንት ማረጋገጣቸውን ዘገባው ጨምሮ አስታውቋል።