(ኢሳት ዜና–መስከረም 15/2010) የጸጥታ ሃይሎች ወገን ለይተው በድንበር ግጭት መሳተፋቸው የሀገራችንን አንድነትና የሕዝባችንን ሰላምና ደህንነት አስጊ እንዳደረገው ኢሶዴፓ ገለጸ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቻ ከወሰን አካባቢ ግጭቶች ርቀው በሚኖሩ አካባቢዎች የሚካሄደው ግድያና ማፈናቀል ተጠናክሮ መቀጠሉ እንዳሳሰበውም ኢሶዴፓ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያን አንድነትና የሕዝባችንን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ከሁሉም ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም ባለፉት 26 የኢህአዴግ የአገዛዝ አመታት ሕዝባችንን ከፋፍሎ የሚገዛበት ስልቱን እየቀየሰና እየተገበረ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንደዚሁም አጎራባች ክልሎች እርስ በርስ የሚጋጩበትን ሁኔታ ፈጥሮ በመቆየቱ የሀገራችንን አንድነትና የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ጥሎት ይገኛል ብሏል።
ይህ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሊቀመንበርነት የሚመራው ፓርቲ በኦሮሚያና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ተቀስቅሶ እስከ አሁን መፍትሄ ሳይሰጠው ለወራት በቆየው ግጭት ከ400 በላይ ዜጎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን ገልጿል።
ከ1 ሚሊየን በላይ ዜጎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል ይላል መግለጫው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም 18 የሚደርሱ የጉጂ ኦሮሞች፥የቡርጂና የሲዳማ በሄር አባላት እንደተገደሉና በርካታዎቹም እንደቆሰሉ የፓርቲው መግለጫ ያሳያል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ከወሰን አካባቢ ግጭቶች ርቀው በሚኖሩ አካባቢዎች የሚካሄደው ግድያና ማፈናቀል ተጠናክሮ መቀጥሉ እንዳሳሰበውም ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳትና በብዙ ሚሊየን ብር የሚገመት በማሳ ላይ የነበረና ያልተሰበሰበ ምርት መዘረፉ ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ግጭት በመስፋት ለሀገሪቱ አንድነት፣ለህዝቡ ሰላምና ደህንነት አስጊ የሆነበት ምክንያት የአገዛዙ ባለስልጣናት፣ካድሬዎችና የጸጥታ ሃይሎች ወገን ለይተው ሰላማዊ ሕዝብን እያጠቁና እያስጠቁ በመሆኑ ነው ይላል መግለጫው።
ፓርቲው በእነዚህ አካላት ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድና ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ አሳስቧል።
ዜጎች ክልሉ የሚጠራበት ብሔር አባል ባለመሆናቸው ብቻ ለብዙ አመታት ቤት ንብረት አፍርተው ከኖሩበት አካባቢ ለተፈናቀሉት ዜጎች ለደረሰባቸው ጉዳት ተገቢው ካሳ በመንግስት ተከፍሏቸው ተፈናቃዮቹ በየመኖሪያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ መደረግ እንዳለበት መግለጫው ያሳስባል።