ኢሳትና የአሜሪካ ድምጽን በፍርድ ቤት ለመክሰስ በሰሜን አሜሪካ የትግራይ ማህበር ውሳኔ አሳለፈ
(ኢሳት ዜና የካቲት 7 ቀን 2010ዓ/ም) የትግራይ ተወላጆች ማኅበር በሰሜን አሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ እኤአ ጃንዋሪ 27 ቀን 2018 ባደረጉት ስብሰባ፣ ኢሳትና ቪኦኤ አማርኛ ዝግጅት ክፍል በቀጥታና በተዘዋዋሪ በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሚያደርጉ በመሆናቸው ሕጋዊና ዲፕሎማሲዊ ዘመቻ እንዲደረግባቸው ሲል ውሳኔ አሳልፏል። የማኅበሩ አባላት በመላው ኢትዮጵያ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል።
“በተለይም በሚዲያ በሚደረገው በትግራይ ብሄር ተወላጆች ላይ ለሚፈጸመው የዘር ጥቃቶች በቀዳሚነት በቀጥታ ተጠያቂው ሚዲያ ኢሳት ነው” የሚለው የአቋም መግለጫው፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ቪኦኤ አማርኛ ዝግጅት ክፍል ውስጥ የሚሰሩ አንዳንድ ግለሰቦችና ሚዲያዎች በሕግ ለመጠየቅ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ውሳኔ አሳልፏል። የሚመለከታቸው አካላት በየአካባቢያቸው በሚገኙ የሕግ ተቋማት በመጠቀም በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የዲፕሎማሲ ስራዎቻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሲሉ አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ባለሃብቶች ለወደመባቸው ንብረቶች በክልልና በፌደራል መንግስት ካሳ እንዲሰጣቸውና ጥቃት የደረሰባቸውም በሕግ እንዲጠየቁ ብለዋል። የትግራይ ተወላጆች ማኅበር በሰሜን አሜሪካ የህወሃት ኢህአዴግ ታጣቂዎች በመላው ኢትዮጵ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚወስደውን ኢፍትሃዊ የመብት ጥሰቶች ሳያወግዙ ዘለውታል።
ማኅበሩ ከዚህ ቀደም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ከሶማሊያ ሲፈናቀሉ በዝምታ በማለፍ የሶማሊያዊያን ተወላጎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ተገደሉ በሚል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።