ኢህአዴግ ያሰባሰበው የህዝብ ድምጽ ” አስፈሪ” ነው ተባለ

ሐምሌ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ምርጫ 2007ትን መቶ በመቶ በሆነ ድምጽ አሸንፊያለሁ ብሎ ያወጀው ኢህአዴግ፣ ከምርጫው በሁዋላ ያሰባሰበው የህዝብ አስተያየት ለፓርቲውም ሆነ ለአገሪቱ ህልውና አስፈሪ መልእክት የያዘ ነው ሲል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። ሪፖርቱ በመጪው ነሃሴ በሚካሄደው የግንባሩ ጉባኤ ላይ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ህዝቡ በአስተዳዳር፣ በፍትህ፣ በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች፣ በውሃና በመብራት እጦት እየተሰቃየ መሆኑን ተጠናክሮ በቀረበው ሪፖርት ላኢ ገልጿል። ከሁሉም በላይ ሙስናና ዘረኝነት አገሪቱን ወደ አስከፊ ጎዳና እየወሰዱዋት መሆኑን የገለጸው ሪፖርቱ፣ በተለይም በኦሮምያና አማራ ክልሎች የተሰባሰበው መረጃ ግንባሩም ማስደንገጡን ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ዘጋቢያችን ገልጿል።
ኢህአዴግ በትምህርት እና በጤና ረገድ የተሻለ ስራ ሰርቷል ብሎ ህዝብ እንደሚያምን የሚያሳየው ሪፖርት፣ በሌሎች ጥያቄዎች ዙሪያ ህዝቡ አሉታዊ መልስ መስጠቱንና በስርአቱ መማረሩን አመላክቷል።
ሁለተኛውን የ5 አመት እቅድ ተንተርሶ በተዘጋጁ የህዝብ መድረኮች ላይ የተሰጡት አስተያየቶች ፣ በድብቅ ከተሰበሰቡት መረጃዎች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ሆነው መገኘታቸውንም የገለጸው ዘጋቢያችን፣ ግንባሩ የህዝብ አስተያየቱን ተቀብሎ መሰረታዊ የሆነ የፖሊሲ ለውጥ ያደርጋል ተብሎ እንደማይጠበቅ አስተያየቱን አስፍሯል።