መስከረም ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የደህንነት ሰዎችም በድጋሚ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ውሎና አዳር መከታተል መጀመራቸውን ለጋዜጠኛው ቅርበት ያላቸው የዓይን እማኞች ገልጸውልናል፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን እንደገለጠው በዛሬው እለት የደህንነት ሰዎች በአካባቢው ባይታዩም እስካለፈው ቅዳሜ ድረስ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ሲከታተሉት እንደነበር ገልጧል። የኢሳት ዘጋቢ ከጋዜጠኛ ተመስገን ጋር ቃለምልልስ በሚያደርግበት ወቅት ስልኩ በተደጋጋሚ እየተቋረጠ ሲቸገር መዋሉን ገልጧል።።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን የአቶ መለስ ተተኪ አድርጎ የመረጠው የኢህአዴግ መንግሥት ጋዜጠኞቹን የማሰር ቁርጥ ውሳኔ ያስተላለፈው ባለፈው ዕረቡ መስከረም 16 ቀን 2005 ዓ.ም ነው ያሉን ምንጮቻችን የቀድሞው ዐቃቤ-ሕግ እና በአሁኑ ጊዜ የአቶ በረከት ስምዖን ረዳት ሆነው በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በሚንስትር ዴኤታ ማዕረግ ገዢው ፓርቲንና መንግሥትን እያገለገሉ ያሉት አቶ ሽመልስ ከማል በጋዜጠኛ ተመስገንና በፍትህ ጋዜጣ አዘጋጆቹ ላይ የሚቀርበውን ክሥ ‹‹ድራፍት›› እንዲያሻሽሉ በፍትህ ሚንሥትር ታዘው ወንጀል ለማዘጋጀት ደፋ- ቀና በማለት ላይ ናቸው ፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር የአቶ መለስ ዜናዊ ዜና እረፍትን የኢህአዴግ መንግስት ገና ገሃድ ባላወጣበት ወቅት እውነታውን በዜና ዘገባው ላይ የገለጸው ፍትህ ጋዜጣ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የሠላሳ ሺህ ኮፒ ክፍያ ፈጽሞ በህትመት ላይ ሳለ በማተሚያ ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች ህትመቱ እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን ከአንድ ቀን በኋላ የማተሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እንዲታተም ፈቅደናል ብለው የጋዜጣው ህትመት ቢቀጥልም ገና ከማተሚያ ቤቱ ሳይወጣ በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ጋዜጣው ከሥርጭት ተቋርጦ በመንግሥት እንዲወረሰ መደረጉና ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም ለአምስት ቀናት ታስሮ መለቀቁ እና የመንግሥትና የግል ማተሚያ ቤቶች ፍትህ ጋዜጣን ለማተም ባለመፍቀዳቸው ህትመቱ መቋረጡ ይታወሳል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቅርቡ ለተወስኑ ቀናት ወደ እስር ቤት ተልኮ የነበረ ቢሆንም የአቶ መለስን የቀብር ስነስርአት ትኩረት እንዳያገኝ ያደርጋል በሚል ምክንያት መፈታቱ ይታወሳል።
በአንባብያን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበራት ፍትህ ጋዜጣ ፣እንዳትታም መታገዷን ተከትሎ የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነቸው ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣም ተመሳሳይ እጣ እንደገጠማት ይታወቃል።
በአሁኑ ጊዜ በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችት የሚያቀርቡ ጋዜጦች በሙሉ ከገበያ እንዲወጡና አገዛዙን ብቻ የሚደግፉ እንደ ሪፖርተር የመሳሰሉ ጋዜጦች ገበያውን እንዲቆጣጠሩ መደረጉ ይታወቃል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide