ኢህአዴግ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢቀርብበትም ለህዝቡ የሚሰጠውን የግዳጅ የፖለቲካ ስልጠና ቀጥሎበታል

መስከረም ፲፪(አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ገዢው ፓርቲ ለመጪው ምርጫ በሚያደርገው ዝግጀቱ የመንግስት ሰራተኞችን፣ መመህራንና ተማሪዎችን በማስገደድ የሚሰጠው የፖለቲካ

ስልጠና እንደቀጠለ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንትም በርካታ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

በአዲስ አበባ በኢትዮ-ቻይና ቲቪቲ በነበረው ስልጠና ላይ ” ከ23 አመታት በሁዋላ አሁንም እራሳችሁን ከደርግ ጋር እያነጻጸራችሁ ነው? ደርግ ከሻእቢያ፣ ከእናንተ ጋርና ከሶማሊያ ጋር ጦርነት ውስጥ

ሆኖ የቴክኒክና የንድፈሃሳብ ማሰልጠኛዎችን ገንብቷል፣ በእናንተ ጊዜ የተሰራው የት ነው? በደርግ ጊዜ ሰዎች በፖለቲካ ምክንያት ብቻ ነው የሚሰደዱት በእናንተ ጊዜ ግን በፖለቲካም በኢኮኖሚም

እየታሰደዱ ነው” የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ የመድረክ አመራሮች የባቡር ግንባታውን በማንሳት ከደርግ የተሻለ መስራታቸውን ለማስረዳት ሞክረዋል። ተማሪዎች በበኩላቸው የባቡሩ ግንባታ

የቅንጅት መሪዎች በ1997 ምርጫ ወቅት አንስተውት የነበረ ሃሳብ እንጅ የእናንተ አይደለም በማለት መልሰዋል።

አንዱ ተሰብሳቢ ከኮርያና ጃፓን ተሞክሮዎችን እንደምትወስዱ ሁሉ፣ ሙስናን በተመለከተስ ከቻይና ተሞክሮ ብትወስዱ ኖሮ ሁላችሁም በስቅላት ታልቁ  ነበር ብሎ በመናገሩ ተወያዩን አስፈግጓል።

በዚህ ግቢ ውስጥ በሚደረገው ስልጠና አንደኛው ቡድን አለመናገር ዲሞክራሲ ከሆነ አንናገርም በሚል ዝምታን መርጠዋል።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ በተካሄደው የተማሪዎች ስልጠና ደግሞ ” ጎንደር ላይ የነበረውን መጠባበቂያ ጄኔረተር ህወሃት ለምን ወሰደው? ዜጎቻችን ለምን በሰው አገር ይሸጣሉ? የአገር ጉዳይ በገዢው ፓርቲ

ብቻ ይፈታል ወይ? ተቃዋሚዎችስ አገራቸው አይደለም ወይ? የሊበራሊዝምን ፍልስፍና ለምን አንከተለም? ” የሚሉት ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣  ተማሪዎች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በተመለከተ

ጥያቄዎችን ሲያነሱ መድረክ መሪዎቹ፣ “ከአንተ ጋር በሁዋላ እንገናኛለን” በማለት ለማስፈራራት መሞከራቸውን ተማሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በያዝነው ዓመት ከስምንት ወራት በኃላ ያካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እያደረጉ ያሉት ዝግጅት ደካማ መሆኑን ጉዳዩ ያሳሳባቸው ወገኖች ጠቁመዋል፡፡

ምርጫውን ያለተቀናቃኝ ለማጠናቀቅ ገዥው ፓርቲ ከህግና ስርዓት ውጪ የመንግስት ሐብት በመጠቀም ጭምር ቅስቀሳ

ከወዲሁ መጀመሩን ለተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለሕዝቡ በተከታታይ በፖሊሲ ማስተዋወቅ ስም የሚካሄዱ ውይይቶች የዚሁ ቅሰቀሳ አካል መሆናቸውን አስታውሰው በተቃዋሚዎች በኩል ግን የሚታይ

አንድም የምርጫ ቅድመዝግጅት አለመኖሩ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዘንድሮ ምርጫ አፈጻጸም ጊዜ ሰሌዳ በቦርዱ በኩል እስካሁን ይፋ ባይደረግም በምርጫው ለመሳተፍ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ዕጩ ማቅረቢያ ጊዜ ከሶስት ወር ያልበለጠ ይቀረዋል ተብሎ እንደሚገመት፤

ነገርግን አቅም አላቸው የሚባሉት አንድነት፣መኢአድ፣ሰማያዊ እና መድረክ የመሳሰሉ ፓርቲዎች ይህን ተገንዝበው በቂ ስራ ሲሰሩ አለመታየታቸው እንዳሳሰባቸው የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ገልጿል።

አንዳንድ ፓርቲዎች በዚህ ወቅት ተቀናጅቶ ወይንም ግንባር ፈጥሮ ለምርጫው ከመዘጋጀት ይልቅ በጥቃቅን የውስጥ

ሽኩቻዎች መጠመዳቸው መጻኢ ዕድላቸውን እንዳያጨልም እነዚሁ ወገኖች ሥጋታቸውን ተናግረዋል።