ኢህአዴግ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሩን በመያዝ እየገመገመና እያሰለጠ ነው

መስከረም ፰(ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦህአዴድ፣ ብአዴን፣ ኢህዴንና ህወሀት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ካለፈው እሁድ ጀምሮ በየክልሎቻቸው ተሰባስበው ግምገማ እያደረጉና ስልጠናም እየወሰዱ መሆኑን ከድርጅቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለ10 ቀናት በሚቆየው ስልጠና አመራሮቹ እርስ በርስ ከመገማገም ባለፈ ስለ ልማት ሰራዊት አደረጃጀት፣ ስለ አንድ ለአምስት  አተገባበር ፣ አክራሪነትና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም በመጪው አመት ስለሚካሄደው አገራቀፍ ምርጫ ስልጠናዎች እና ውይይቶች ይካሄዳሉ።

ተመሳሳይ ስልጠናዎችና ግምገማዎች በከተሞችና በገጠሩ ክፍል ለሚገኙ የግንባሩ አባላት እየተሰጠ ነው። ከጉባኤ ተሳታፊዎች ለመረዳት እንደተቻለው ኢህአዴግ በመጪው ምርጫ  እንደሚያሸንፍ ቢያውቅም፣  በምርጫ 97 ወቅት የተከሰተው አይነት ውዝግብ ሊከሰት ይችላል ብሎ በመፍራቱ ተከታታይ ስልጠናዎችን ለመስጠት አቅዷል።

ከአንድ ወር በፊት በዩኒቨርስቲዎች የኢህአዴግን የአንድ ለአምስት አደረጃጀት ለማስረጽ ከዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶችና ከፍተኛ አመራሮች ጋር በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በእነ አቶ በረከት ስምኦን የተሰጠው ስልጠና እንዳለቀ አሁን ደግሞ የ2ኛ ደረጃ ርእሰ መምህራን በመሰብሰብ የተለያዩ ስልጠናዎችን እና ግምገማዎችን እያደረገ ነው።

ከርእሰ መምህራን ጋር የሚደረገው ውይይት ዋና ዋነ ርእሶች የ2005 ዓም የትምህርት አፈጻጸም ግምገማ፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው የልማት ሰራዊት አደረጃጀት፣ አክራሪነትና መገለጫዎቹ፣ ወጣቱ ላይ ስለተሰሩ ስራዎች፣ ጸረ-ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች እና መገለጫቸው እንዲሁም የትምህርት ጥራት የሚሉት ይገኙበታል።

በአገሪቱ ያለው ወጣት በኢህአዴግ አመራር እየተከፋ መምጣቱ ግንባሩን እንዳሳሰበው ከተወያዮች ለመረዳት ተችሎአል። በያዝነው አመት ወጣቱን ለመያዝ በሚል መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦ ለመንቀሳቀስ አቅዷል።

ኢህአዴግ ተመሳሳይ ግምገማዎችንና ስልጠናዎችን ከተለያዩ መስሪያ ቤት ሰራተኞችና ከወጣቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቻው ከሚላቸው ድርጅቶች ጋር ለመስራት እቅድ ይዟል።