ኢህአዴግ ከሚያደርገው የካቢኔ ሹምሽር አዲስ ነገር ላይጠበቅ ይችላል ተባለ

መስከረም ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፊታችን መስከረም 24 ቀን በኢህአዴግ መቶ በመቶ የተያዘው ፓርላማ ስራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የአቶ
ሃይለማርያም የጠ/ሚኒስትርነት ሹመት ካጸደቀ በሃላ በጠ/ሚኒስትሩ አቅራቢነት የሚካሄደው የካቢኔ ሹም ር አዲስ ነገር ይዞ አይመጣም ተብሎአል። ለግንባሩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለአዲስአበባው ዘጋቢያችን እንደተናገሩት ግንባሩ በሙስናና በመልካም አስተዳደር ችግሮች በተጨማለቁ የካቢኔ አባላት ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ካልቻለ ለህልውናው አስጊ ነው፡፡ ሕዝቡ በአሁኑ ሰዓት ባለው ስርዓት እጅግ የተማረረበት ወቅት ላይ መሆኑን የጠቀሰው አባሉ፣ ባለፈው ግንቦት ወር ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ባልተካሄደበትም ሁኔታ ጥቂት የማይባል ሕዝብ ኢህአዴግን አለመምረጡ በቂ ማሳያ ነው ብሏል፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ ሶስት ዓይነት አሰላለፍ የያዘ ሃይል መኖሩን የጠቆመው ምንጫችን፣ አንዱና ዋናው በሙስናና ብልሹ አሰራር ራሱን ያበለጸገ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ራሱን አብዮታዊ ዴሞክራት አድርጎ የሚቆጥረውና ሙሰኞችን የሚቀናቀነው ሃይል ነው፡፡ ሶስተኛው ቡድን መካከል ላይ ሆኖ ወዳመዘነበት የሚያጋድል ወላዋይ አቋም ያለው መሆኑ በግንባሩ ታምኖበታል ያለ ሲሆን ፣ እነዚህ ሃይሎች እርስበእርስ የሚደርጉት ፍልሚያ በአሁኑ ሰዓት አፍጥጦ እየታየ ነው ሲል ያክላል።
ኢህአዴግ በርካታ ባለስልጣናቱ፣
ከፍተኛ ስልጣን ላይ ሆነው በሙስና የተዘፈቁ ፣ በጥቅም የተሳሰሩ፣ ከፍተኛ የገንዘብና የጥቅም ቡድኖችን ከላይ እስከታች መፍጠር የቻሉ በመሆናቸው ግንባሩ በቀላሉ ማስወገድ የሚችልበት አቋም ላይ አለመሆኑን የጠቀሰው አባሉ፣ የመልካም አስተዳደርና የጸረ ሙስና ዘመቻ መፈክሮች እንደከዚህ ቀደሙ ከመፍክርነት ሳያልፉ የሚከስሙ ናቸው ብሎአል፡፡
የፖሊስ፣ የመከላከያና የደህንነት ተቋማትን ጨምሮ በሁሉም መንግስታዊ ተቋማት በሙስናና ብልሹ አሰራር የራሳቸውን መንግስታዊ መስመር የዘረጉ ሹማምንት የሰዎችን ሰብኣዊ መብት የሚጥሱ፣ እንደፈለጉ የሚያስሩና የሚፈቱ በመሆኑ ስርዓቱን አደጋ ውስጥ እንደጣሉት መናገሩን ዘጋቢያችን በላከው ዘገባ ጠቅሷል።