ኢህአዴግ በደንብ አላገለገሉኝም ያላቸውን የመጅሊስ አመራሮችን አባረረ

የካቲት ፲፮(አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከሕዝበ ሙስሊሙ ፍላጎት ውጪ በ2005 ዓ.ም የተመረጡት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) አመራሮች የመንግስትን ፍላጎት ማርካት  ባለመቻላቸውና በአመራሮቹ ላይ እምነት በመጥፋቱ በአስቸኩዋይ ስልጣናቸውን እንዲያስረክቡ በማድረግ በምትካቸው ሌሎች ተመርጠዋል።

በአሁኑ ወቅት በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ሼህ ኪያር መሐመድ ኢማንን ወደ ስልጣን ያመጣውን የመጅሊስ ምርጫ  ሕገወጥ ነው በማለት እንዲታገድ ለከፍተኛው ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ሰባተኛ ፍትሐ ብሄር ችሎት በወቅቱ  ክስ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ክሱ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶአል፡፡

11 አባላት ያሉት የቀድሞ መጅሊስ አባላት ለኢህአዴግ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት አልሰጡም በሚል የሥራ አስፈጻሚ አባላትን በማስፈራራትና የኡላማዎች ም/ቤትን አንዳንድ ተለጣፊ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎችን በማስተባበር በፍጥነት ምርጫ እንዲካሄድ በተወሰነው መሰረት አስቸኳይ ጉባዔው ተካሂዷል።

አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውም  ሐጂ መሀመድ አሚን ጀማልን ፣ ከኦሮሚያ ክልል፣  ፕሬዝዳንት አድርጎ የመረጠ ሲሆን የአማራ ክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ተወካይ ሼህ ዑመር ይማም የጠቅላይ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፣ የአዲስ አበባው ተወካይ ሐጂ ከድር ሁሴን ዋና ፀሃፊ ሆነው እንዲሰሩ ተመርጠዋል። ጠቅላላ ጉባዔው ቀደም ሲል የነበሩትን አመራሮችን ሙሉ በሙሉ በማንሳት በአዲስ እንዲተኩ አድርጎአል፡፡

የቀድሞ አመራሮች መጀመሪያውኑም የሕዝበ ሙስሊሙን ፍላጎት መሰረት አድርጎ በተካሄደ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደሃላፊነት እንዳልመጡ የሚታወቅ ቢሆንም በእሁዱ ምርጫ ወቅት አመራሮቹ ከሃላፊነታቸው የተነሱት “የህዝበ ሙስሊሙን የልማት ጥያቄ አልመለሱም፣ አክራሪነትና ጽንፈኝነትን የመታገል ቁርጠኝነት አላሳዩም” በሚል መሆኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ኢሳት አሁን የተሾሙት የመጅሊስ አመራር አባላት ከመንግስት የደህንነት ሃይሎች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ የሚያሳይ ከስብሰባ ላይ በድብቅ የተቀረጸ ድምጽ መልቀቁ ይታወቃል። ገዢው ፓርቲ ሙስሊም ወጣቶችን እንዳዲስ በመያዝ እያሰረ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። የፌደራል ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በቅርቡ በባህርዳር ባደረጉት የክልሎች የጸጥታ ግምገማ ላይ ፣ መንግስት በመጅሊስ አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ፍንጭ ሰጥተው ነበር።