ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ለደረሰው የሰውና የንብረት ውድመት ከፍተኛ አመራሩ ተጠያቂ ነው አለ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ/ም) በኢትዮጵያ ለደረሰው የዜጎች እልቂት፣ የሚሊዮኖች መፈናቀልና ከፍተኛ ንብረት ውድመት የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ሃላፊነቱን ይወስዳል ሲል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ድርጅቱ ሰሞኑን በሰጣቸው ተከታታይ መግለጫዎች፣ በኢትዮጵያ ለሚታዬው የጸጥታ መደፍረስ የቀለም አብዮት እንዲካሄድ የሚፈልጉ የምዕራብ አገራትንና ኤርትራን ተጠያቂ አድርጎ ነበር። ዛሬ ባወጣው መግለጫ ደግሞ “በክልሎችም ሆነ በክልሎች መካከል በልዩ ልዩ ሰበቦች የሚከተሰተው የሰላም መደፍረስ ለዜጎቻችን አሳዛኝ ሞት መበራከትና መቁሰል እንዲሁም ከባድ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡
በተጨማሪም ከፍተኛ የንብረት ውድመትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መገታት አስከትሏል፡፡ ይህ ለረጅም አመታት በሰላም በኖረችው አገር ውስጥ የስጋት መንፈስና ጭንቀት ፈጥሯል፡፡ በየቦታው እየተነሱ ያሉ ግጭቶች ከሰው ሞትና ከንብረት ውድመት በዘለለ የሃገራዊ ሕልውናችን ለአደጋና ሕዝባችንን ለጥፋት ቋፍ ያደረሱበት ሁኔታ ከመኖሩ በላይ ለውጭ ጥቃት ተጋላጭነታችንን የመጨመር ውጤት አስከትለዋል፡፡” ብሎአል።
እነዚህ ሁሉ ችግሮች “ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱና የድርጅትና የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች በተናጠልና በጋራ፣ ስትራተጅያዊና ታክቲካዊ አመራር የመስጠት ሃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው የተፈጠረ ችግር ነው፡፡” ያለው ኢህአዴግ መግለጫ፣ “ከፍተኛ አመራሩ ችግር አስቀድሞ የመለየት፣ ተንትኖ የማወቅ፣ የመፍቻ መንገዶች የመተለምና በዚሁ መሠረት የመፍታት ብቃቱ ወቅቱና መድረኩ ከሚጠይቀው ደረጃ ጋር አብሮ ባለማደጉ የተወሳሰበውን አገራዊ መድረክ በብቃት የመምራት ጉድለት እንደነበረበት የጋራ አቋም ተይዟል፡፡ “ ብሎአል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ በአጠቃላይ ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና ለደረሰው የንብረት ውድመት ሃላፊነት እንደሚወስድ ቢናገርም፣ ከአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በስተቀር ሌሎች የስራ አስፈጻሚ አባላት ስልጣናቸውን ሳይለቁ በአመራር ላይ መቆየትን መርጠዋል።
ኢህአዴግ በመግለጫው በኦሮሞ ብሮድካስቲንግና በአማራ መገነኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ፍንጭ ሰጥቷል። “ በክልልም ይሁን በፌዴራል ያሉ የህዝብ የሚዲያ አውታሮች ሕግና ሥርዓትን ጠብቀው የማይሠሩበት ሁኔታ እያመዘነ የህዝቡን ሰላምና አብሮ የመኖር ገንቢ ባህል የሚሸረሽሩ ሰበካዎች የሚሰጥባቸው፣ ብሎም ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጩ አጥፊ ቅስቀሳዎች የሚካሄድባቸው እየሆኑ ለመምጣታቸው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚም ሆነ የሚመራው መንግሥት ድክመት አስተዋፅኦ “ አድርጓል የሚለው መግለጫው፣ በእነዚህ የሚዲያ ተቋማት ላርምጃ ይወሰዳል ብሎአል።
ኢህአዴግ በእያካባቢው የሚደረጉ መንገድ የመዝጋት እና ሌሎችንም ተቃውሞዎች በሚያደርጉ ሃይሎች ላይ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል ገልጿል። በሌላ በኩል ደግሞ “በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶችና ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመቅረፍ” እንደሚንቀሳቀስ ገልጿል። ኢህአዴግ ከሁሉም ተቃዋሚዎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ ቢልም፣ በውጭ ከሚገኙና ትጥቅ ትግል ከሚያደርጉ ሃይሎች ጋር ለመነጋገር ፍላጎት ይኑረው አይኑረው በዝርዝር አላብራራም።
እንዲሁም “ምሁራንና የሲቪክ ማህበረሰቦች ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ተገቢ ሚናቸውን የሚጫወቱበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ወስኛለሁ” በማለት መግለጫው ላይ ያካተተ ቢሆንም፣ አፋኙን የሲቪል ማህበራትን ህግ ስለማሻሻል ወይም ስለመለወጥ ምንም ያለው ነገር የለም።
ኢህአዴግ በመግለጫው ሰሞኑን ሲያደርገው እንደነበረው አንድም ቦታ ላይ ስለ ውጭ ሃይሎች አላነሳም።
የአለማቀፍ ማህበረሰቡና የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ኢህአዴግ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር አዲስ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።