ኢህአዴግ በአገራዊ ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች ዙሪያ ለመምህራን ገለጻ እየሰጠ ነው

መስከረም ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ መንግሥት ከቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2005 ዓ.ም  ጀምሮ በሀገሪቱ የሚገኙ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንን ለትምህርት ጥራት ምክክር ብሎ ለአንድ ሣምንት የሚቆይ ሥልጠና በየትምህርት ቤቱ በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡

ቅዳሜ እና እሁድን በትምህርት ጥራት ላይ ያወያዩት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይለሥላሴ ፍሰሃ ናቸው ሲል ለዘጋቢያችን የገለጸው አንድ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር ፕሮግራሙ ኃላፊው በፕላዝማ በሚያደርጉት ዲስኩር የሚጀመር ሲሆን በየትምህርት ቤቱ አወያይ ተደርገው የተቀመጡ ካድሬዎችና በተለያዩ ቦታዎች የሚቀመጡ የኢህአዴግ አባላት መምህራን አስተኳሽ ጥያቄዎችን በማንሳት የፈለጉትን አጀንዳና መልዕክት ያስተላልፋሉ በማለት ተናግሯል፡፡

በዛሬው ዕለት ግን ከትምህርት ጥራት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የሃይማኖት አክራሪነት አጀንዳ ሆኖ የቀረበ ሲሆን ዋና ዓላማውም በአሁኑ ጊዜ መብታቸውን ለማስከበር በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት የሙስሊሙ ማህበረሰቦች ላይ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ተገቢነት ያለው ነው ወደሚል መደምደሚያ ወስደውታል በማለት መምህሩ አስረድቷል፡፡

በነገው ዕለትም ኢህአዴግና መንግሥት በመተካካት ሂደት የደረሱበት ዕመርታ የውይይት መነሻ የሚሆን ሲሆን የዚህ ውይይት ዋና ዓላማውም ማህበረሰቡ እየተከናወነ ያለውን መንግሥትን እና ሥልጣንን የማረጋጋት ሥራ በአወንታዊ ጎኑ እንዲወስደውና በሰፊው ህብረተሰብ ቅቡል እንዲሆን ለማድረግ መሆኑ የትምህርት ቢሮ ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide